ጥብቅ እንደሆነ የሚነገርለት የኢትዮጵያ የባንኮች ብድር አሰጣጥ ሥርዓት አሁንም ሊሻሻሉ የሚገቡ ጉዳዮች ያሉበት ነው ተባለ።
- 5 hours ago
- 1 min read
ሐምሌ 27 2018
ጥብቅ እንደሆነ የሚነገርለት የኢትዮጵያ የባንኮች ብድር አሰጣጥ ሥርዓት አሁንም ሊሻሻሉ የሚገቡ ጉዳዮች ያሉበት ነው ተባለ።
ሰዎች ከዚህ በፊት የወሰዷቸውን ብድሮች የከፈሉበት መልካም ታሪክ እየታየ ከባንኮች ገንዘብ የሚያገኙበት ሥርዓት በኢትዮጵያም ሊለመድ እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የባንኮች ብድር መመርያና ፖሊሲ ከባንክ ባንክ የተለያየ በመሆኑ የብድር አሰጣጥ ሂደቱም በተወሰነ መልኩ ከተቋም ተቋም እንደሚለያይ ተነግሯል፡፡
ከብድር ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ያሉ ባንኮች ዋና ዋና የብድር መስፈርቶችን ያስቀምጣሉ፡፡
ከእነዚህ መካከል የብድር መያዣ ፣ ካፒታል፣ የስራ ዕቅድ፣ የገንዘብ አቅም ፣ የብድር ስጋት ደረጃ እንዲሁም አስፈላጊ የሰነዶችና ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት የሚሉት እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
ሆኖም እነዚህን ነገሮች በዘመናዊ መልክ ማረጋገጥ የሚቻልበት መንገድ ቢዘረጋ ሲሉ በጉዳዩ ላይ ያነጋገር ናቸው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
ከጥብቅ መስፈርቶቹ መካከል አንዱ የብድር ታሪክ ሲሆን እነዚህን እና የተበዳሪው አቅም ምን ድረስ ነው የሚለውን ሌሎች ሀገራት እንዴት እንደሚያስኬዱት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዘሪሁን ጴጥሮስ ነግረውናል፡፡
በሌሎች ሃገራት እያንዳንዱ ሰራተኛ በቀጥታ በበይነ መረብ አማካኝነት እንደሚመዘገብና የተበዳሪው የገንዘብ አጠቃቀሙ፣ የውጪ አጠቃቀም ፣ ገቢው ምን ያህል ነው፣ የሚለው እያንዳንዱ እንቅስቃሴው በካሜራ በመታገዝ እንደሚጠና አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በመነሳት እንደ ሀገር ቢሰራበት ያሉትንም ሀሳብ አክለዋል፡፡
ይህ ሁሉ የሚሆነውና መዘመን ያስፈልገዋል የሚባለው ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ለመለየትና ቀድሞ ለመከላከል እንደሆነ ባለሙያው ዘሪሁን ጴጥሮስ ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ በቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ጥናታቸውን ያቀርቡት በዩንቨርስቲው የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ መምህርና ተመራማሪ ነዋይ አያሌው ትልልቅ የሚባሉ ባንኮች ኪሳራ ሊያስከትል የሚችል የብድር አሰጣጥ አሰራር እንደሚከተሉ በጥናታቸው ማረጋገጫቸውን ነግረውናል፡፡
ሌላኛው የምጣኔ ሃብት ባለሙያና በባንኩ ዘርፍ ልምድ ያላቸው ሲሳይ ክፍሉ በበኩላቸው ባንኮች ራሳቸው ለኪሳራ አያጋልጡም ለትርፍ እንደመቋቋማቸው ምን ላይ መስራት እንዳለባቸው ያውቃሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለሚሰጡ ብድሮች ባንኩንም በማይጎዳ መልኩ ተበዳሪውም ተጠቃሚ እንዲሆን ይህንን የተመለከቱ ፖሊሲዎች በሚውጡበት ጊዜ ከሚደረጉ ጥናቶችና የምርምር ውጤቶች በመነሳት መዘመንና መሻሻል ያለባቸውን በመለየት ቢሰራበት ሲሉ ባለሙያዎቹ ምክር ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ....
ማርታ በቀለ
_edited.jpg)
