ጥቅምት 8 2018 የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ተቋም ለአንድ ዙር የመድኃኒት ግዥ ለመፈፀም 200 ቀናት እንደሚፈጅበት ተናገረ።
- sheger1021fm
- 3 hours ago
- 1 min read
በዚህም ምክንያት መድኃኒት ተገዝቶ ወደ ጤና ተቋማት እስኪደርስ እስከ 4 ወር ሊፈጅ ይችላል ተብሏል።
የሠላም ዕጦት ችግር ባለባቸው የኦሮሚያ፣ የአማራና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አካባቢዎች ደግሞ ችግሩ ከዚህም እንደሚከፋ ተነግሯል።
ተቋሙ የመድኃኒት አገልግሎት አዋጅ እንደ አዲስ ከተሻሻለ በኋላ ለ #መድኃኒት ግዢ የሚወስድብኝ ጊዜ በፊት ከነበረው በግማሽ ቀንሷል ቢልም የክልል የጤና ተቋማት ግን አሁንም በመድኃኒት አቅርቦት መዘግየት እየተፈተንን ነው ብለዋል።
ይህ የተባለው በ7ኛው ብሔራዊ የመድኃኒት አቅርቦት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ነው።

በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ወደ ኃላፊነት የመጡ ሰሞን በህዝብ እንደራሴዎች በኩል የሚቀርብላቸው ጥያቄ ሁሉ የመድኃኒት አቅርቦት እንደነበር ተናግረዋል።
በዚህም ማህበረሰቡ በመድኃኒት አቅርቦት ምን ያህል እየተፈተነ እንደሆነ ተረድተን ሰፊ ስራዎችን እየሰራን ነው ብለዋል ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ።
የሃገር ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦትን ለማሻሻል ለሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ያሉ ሲሆን ኢትዮጵያ 12 የግል የህክምና መሳሪያና መድኃኒት አምራች ፋብሪካዎች እንዳሏት ጠቅሰዋል።
በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው ሀሳባቸውን ያካፈሉ የመድኃኒት አምራች ማህበር ተወካይ በበኩላቸው የመድኃኒት ማምረቻ ግብዓት በዶላር ገዝተን እያመረትን ነው፣ ግን በብር ስለምንሸጥ ከቀን ወደ ቀን እየሰፋ ባለው የዶላርና የብር ልዩነት እየተፈተንን ነው ብለዋል።
በዚህም ምክንያት 12ቱም የህክምና መሳሪያና መድኃኒት አምራች ፋብሪካዎች ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው እየሰሩ እንዳልሆነ የማህበሩ ተወካይ ተናግረዋል።

የመድኃኒት አቅርቦት ተቋሙ ለሀገር ውስጥ አምራቾች ትኩረት ስለምሰጥ ከ13.4 ቢለየን ብር በላይ የህክምና ግብዓቶች ጨረታ አውጥቼ ከጨረታው አሸናፊዎች የ4.6 ብር የህክምና ግብዓቶችን በመረከብ ድጋፌን እያሳየሁ ነው ብሏል።
7ኛው ሀገር አቀፍ የመድኃኒት አቅርቦት ዓመታዊ ጉባኤ የጤና ተቋማት የመድኃኒት ፍላጎትን ለማሟላትና ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት የሚረዳ ሃሳብ ለማዋጣት የተዘጋጀ መድረክ ነው ተብሏል።
በመድረኩ ላይ የህዝብ እንደራሴ ምክር ቤት ተወካዮች፣ የጤና ሚኒስቴር አመራሮችና የክልል የጤና ቢሮ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ንጋት መኮንን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s