top of page

ጥቅምት 8 2018 - በዚህ ተለዋዋጭ የዓለም ስርዓት አፍሪካ እንዴት ተጠቃሚ ትሁን?

  • sheger1021fm
  • 32 minutes ago
  • 2 min read

በአፍሪካ ሰላምና ደህነት ዙሪያ የሚመክረው የጣና ፎረም የዘንድሮው መድረክ ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ስርዓት አፍሪካ እንዴት ተጠቃሚ ትሁን በሚለው ሀሳብ ዙሪያ ይመክራል ተብሏል።


ለተወሰነ ጊዜያት ተቋርጦ የቆየው የጣና ፎረም 11ኛው መድረክ ከመጪው ጥቅምት 14 እስከ 16 እንደሚደረግ አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡


በዚህ ፎረም ከመላው ዓለም የተወጣጡ የአፍሪካን ቀንድ ሁኔታን የሚከታተሉ ልዩ መልክተኞች፣ የተመድ፣ የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች ቀጠናውን በተመለከተ እንዲወያዩ መጋበዛቸውንም ሰምተናል፡፡


በዚህ በየጊዜው እየተለዋወጠ ባለው የአለም ስርዓት አፍሪካ እንዴት ብትራመድ ተጠቃሚ ያደርጋታል በሚል፣ የአህጉሪቱ መሪዎች፣ ሚኒስትሮች እና የሚመለከታቸው አካላት እንደሚመክሩም ተነግሯል፡፡

ree

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ፎረሙን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ‘’ከዚህ በፊት በነበረው የአለም ስርዓት አፍሪካ ግራና ቀኝ እንደሚጠልዟት ኳስ እንጂ ሯሷ መሪ ተዋናይ ሆና የተጫወተችባቸው የዓለም ስርዓቶች’’ እንደሌሉ አንስተዋል፡፡


በዘንድሮው የጣና ፎረምም አፍሪካ በዓለም ስርዓት ውስጥ ተጠቃሚ ለማድረግ በማለም መሪዎቿ እና የሚመለከታቸው አካላት ይወያያሉ ብለዋል፡፡


እርስ በእርስ መኮራረፍ በሚደጋገምባቸው የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ በጋራ አፍሪካን በዓለም ስርዓት ተጠቃሚ የማድረጉ ነገር ምን ያህል ውጤታማ ሊያደርጋቸው ይችላል ያልናቸው አምባሳደር ዘሪሁን አበበ፤ በሀገራቱ መካከል ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቅሰው ነገር ግን እነዚህ ችግሮች ለመፍታት ይኸው የጣና ፎረም እንደሚረዳቸውም አብራርተዋል፡፡


#የጣና_ፎረም በሰላምና ደህንነት ጉዳይ ተሸፋፍነው የሚታለፉ ጉዳዮችን፤ በጋራም ሆነ በጎንዮሽ ውይይቶች በግልፀኝነት እንዲካሄዱ መድረክ ያመቻቸል ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰላምና ደህንነት ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ሜርሲ ፍቃዱ(ዶ/ር) ናቸው፡፡


እስካሁን የተካሄዱ 10ሩ የጣና ፎረም መድረኮች ለአፍሪካዊያን ምን ጠቀሙ በሚል ከጋዜጠኞች ሀሳብ የተነሳላቸው ሜርሲ ፈቃዱ(ዶ/ር)፤ ጣና ፎረም የውይይት አውዶች የመፍጠር እንጂ ‘’የውሳኔ ሰጪ መድረክ’’ እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ ነገር ግን ለፖሊሲ ጠቃሚ የሆኑ የውይይት ውጤቶችን ሰንዶ እያስቀመጠ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡


ለዘንድሮው የጣና ፎረም “አፍሪካ በተለዋዋጩ ሉላዊ ስርዓት” የሚል ርዕስም ተመርጦለታል ተብሏል፡፡


11ኛው የጣና ፎረም ጥቅምት 14 ቀን በባህር ዳር እንዲሁም ከጥቅምት 15 እስከ 16 2018 ዓ.ም ደግሞ በአዲስ አበባ ይደረጋል መባሉንም ሰምተናል።


ማንያዘዋል ጌታሁን


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page