ጥቅምት 5 2018 - በአዲስ አበባ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ምዝገባ ጥቅምት 1 መጀመሩና እስከ ህዳር 30 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተነገረ
- sheger1021fm
- Oct 15
- 1 min read
ከማህበረሰብ ከሚሰበሰበው መዋጮ በተጨማሪ የከተማ አስተዳደሩ በ2017 ዓ.ም ብቻ ለአገልግሎቱ 1.3 ቢሊዮን ብር ድጎማ አድርጓል ተብሏል፡፡
ጥቅምት 1 የተጀመረው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ምዝገባ ከ2.8 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ተናግሯል፡፡
የቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በ2017 ዓ.ም ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መጠቀማቸውን ተናግረው በዚህ አመትም በተለያየ ምክንያት አገልግሎቱን ያቋረጡትን ታሳቢ በማድረግ ከሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ይመዘገባሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በ2017 ዓ.ም ከ2.8 ሚሊዮን በላይ አባላትና ቤተሰቦቻቸው በተመላላሽ እና በተኝቶ ህክምና ከጤና ጣቢያ ጀምሮ ባሉ የመንግስት ጤና ተቋማት ተጠቃሚ መሆናቸው ተነግሯል፡፡
የ2018 ዓ.ም አባልነት የምዝገባ ወቅትም ከጥቅምት 1 እስከ ህዳር 30 2018 ዓ.ም በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ጣቢያ በሌለባቸው ክፍለ ከተሞች ደግሞ በወረዳዎች ተጀምሯል ተብሏል፡፡

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ፕሮግራሙ የመክፈል አቅምን መሰረት ያደረገ የመዋጮ ስርዓት እንዲኖር የተሻለ የገቢ ያላቸውና በንግድ ስራ ላይ የሚተዳደሩ ሰዎችን ያካተተ እንዲሁም የመክፈል አቅም ለሌላቸው ሰዎች ደግሞ ታሳቢ በማድረግ ዓመታዊ መዋጮዋቸው በመንግስት እንዲሸፍን እየተደረገ ነው ሲሉ ዶክተር ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡
የአገልግሎቱ አባል ለመሆን የመዋጮ ገንዘቡ መጠኑን ጨምሯል የመክፈል አቅምን ያገናዘበ አይደለም በሚል ከተጠቃሚዎች ቅሬታ ይነሳል ለዚህም ቢሮ ያለውን ምላሽ በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሃላፊው ዶክተር ዮሃንስ ጫላ፤ በዚህ ዓመት ያደረግነው ጭማሪ ሳይሆን አዋጁ ላይ የተቀመጠው ነው ከዚህ በፊት ይከፍሉ የነበሩት እንዳላቸው የገቢ መጠን ነው ዝቅተኛ የሆነውን በፊት የሚከፍሉትን ይዘው ነው የሚቀጥለው ብለዋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ የመጣው የህክምና ግብዓት ዋጋን ያማከለ ጥናት ሲካሄድ ጥናቱ የሚያሳየው ከፍተኛ ነው ነገር ግን ህብረተሰቡ ላይ ጫና እንዳይኖር ከማድረግ አኳያ ከተሰበሰበው መዋጮ ላይ የከተማ አስተዳደሩ 1.3 ቢሊየን ብር ድጎማ ማድረጉን ዶ/ር ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s
👔LinkedIn ፡ https://tinyurl.com/tyfaekvx












Comments