ጥቅምት 28፣ 2017 - ከንግድ ቢሮ እውቅና ውጭ በ339 ህገ ወጥ አካውንቶች፤ የኦንላይን ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ሲሰጥ ነበር ተባለ፡፡
- sheger1021fm
- Nov 7, 2024
- 1 min read
ከንግድ ቢሮ እውቅና ውጭ በ339 ህገ ወጥ አካውንቶች፤ የኦንላይን ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ሲሰጥ ነበር ተባለ፡፡
ንግድ ፍቃድ ምዘገባ፣ እድሳት፣ ስረዛ እና ሌሎች በዚሁ ዙሪያ ያሉ አገልግሎቶች ቢሮ በኦንላይን እንደሚከውን ተናግሯል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ይህንን ያለው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡
በተደረገ ዳሰሳ የኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ ፍቃድ ከተሰጣቸው ውጪ 339 ፌክ አካውንቶች የኦንላይን ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ሲሰጡ የተገኙ ሲሆን አገልግሎት ፈላጊዎች ወይም ነጋዴዎች የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን ሳይሟሉ ንግድ ፍቃድ መውሰድ፣ ማደስ፣ የካፒታል ማሻሻያ ማድረግ ተግባር ሲከውኑ እንደነበር ደርሼበታለሁ ብሏል ቢሮው፡፡
በነዚህ ህገ-ወጥ አካውንቶች በርከት ያሉ አገልግሎቶች መሰጠታቸውን የሚናገሩት የቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ ፍሰሀ ጥበቡ በንግድ ህጉ መሰረት መስፈርቱን ያላሟሉ እንዲያስተካክሉ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ይህም ሆኖ ግን 46 የሚሆኑ ሰራተኞች ከፈቃድ ውጭ 263 አገልግሎቶችን ሰጥተዋል የሚሉት ምክትል ሀላፊው ከዚህም ውስጥ 57 አገልግሎቶች ክሊራንስ ሳይወስዱ፣ ኦዲት ሳይደረግ፣ የመመስረቻ ቃለ ጉባኤ ሳይኖራቸው አገልግሎት በማግኘት የመንግስትን ጥቅም ያሳጡ መሆኑ ታውቋል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የኦንላይ አገልግሎቱን ሲጀምር በ11ዱም ክፍለ ከተሞች ከ1200 በላይ አካውንቶች አስከፍቶ ስራዎች ሲከወኑ መቆየቱ የተነገረ ሲሆን በቢሮው ስር የሚፈፀሙ ህገ-ወጥ ድርጊቶችንም ለማስቀረት ከሀምሌ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎቱን በ28 ሰራተኞች ብቻ እንዲከወን ተደርጓል ተብሏል፡፡
ይህም ብልሹ አሰራርን ይቀንሳል ተብሎ ተስፋ እንደተጣለበት የሚናገሩት ፍሰሀ ጥበቡ ከ130 ሺህ በላይ አገልግሎቶች ተሰጥተዋል ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት ከ362 በላይ አገልግሎቶች አሰራርን ባልጠበቀ እና መስፈርትን ባላሟላ መልኩ አገልግሎት መሰጠቱን በኦዲት አረጋግጫለሁ ያለው ቢሮው ከዚህ ውስጥ 32ቱ አገልግሎቶች የመንግስትን ጥቅም ሊያሳጡ የሚችሉ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በምሰጣቸው የኦንላይን አገልግሎቶች 136 የስራ ሃላፊዎች እና ፈፃሚዎች ላይ የተጠያቂነት ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ ነው ተባለ ሲሆን ከ430 አገልግሎቶች በላይ መስፈርት ሳያሟሉ የተሰጡ አገልግሎቶችም ተጠያቂ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ 16 አገልግሎቶችን በኦንላይን እየሰጠሁ ነው ብሏል፡፡
ፋሲካ ሙሉወርቅ











Comments