ጥቅምት 18 2018 - የአየር ንብረት ለውጥን የማቋቋም ግብርናን ለመፍጠር ሲከወን የቆየው የመረጃ ግብዓት የማቅረብ ስራ ተጠናቀቀ፡፡
- sheger1021fm
- 57 minutes ago
- 1 min read
ባለፉት 5 ዓመታት ሲተገበር የነበረው የመሬት፣ አፈር እና የሰብል መረጃን በተመለከተ ሲከወን የቆየው ስራ መጠናቀቁን የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሩዋንዳ መተግበሩን የተነገረ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ የአየር ንብረት ተስማሚ ግብርናን ለመደገፍ ያለመ ነበር ተብሏል።

ስራው በተሰራባቸው አካባቢዎች ስንዴ በሄክታር 15 ኩንታል ይገኝ የነበረ ሲሆን አሁን ወደ 34 ኩንታል አድጓል፣ ጤፍ 22 ኩንታል ደርሷል፡፡
የመሬት፣ የአፈርና የሰብል መረጃ አገልግሎት ፕሮጀክት በምርምር ተቋማት ውስጥ ዘላቂነት ያላቸው የመሬት ፣ የአፈርና የሰብል መረጃ ማዕከላትን ማቋቋምና ሀገራዊ የግብርና እውቀትና ማጠናከር ዓላማ አድርጎ የማሳያ ስራው ሲሰራ ነበር ተብሏል።

እንደ ሀገር የሚታየው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ግብርናውን ማሳደግ ከተፈለገ ዘርፉ በመረጃ መደገፍ አለበት ያሉት የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ(ፕ/ር) ናቸው።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቦርድ ሰብሳቢ አበራ ደሬሳ (ዶ/ር) መሬታችን ለየትኛው የአየር ንብረት ተስማሚ ነው የሚለውን መለየት እና ምን እንደሚያበቅልም መረጃ ያስፈልጋል ብለዋል።
አሁን የተሰራው የማሳያ ስራ ለዚህ ጥሩ ጅምር ነው ያሉ ሲሆን ስራው ዘላቂ በሆነ መንገድ መቀጠል አለበት በማለት ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በሁለት አካባቢዎች በባሶና ወረዳ እና በአዳሚ ቱሉ ጅዶ ኮምቦልቻ በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን ወጥ በሆነ መንገድ እንደ ሀገር ለመተግበር የፋይናንስ ማፈላለግ ስራ መስራት ያስፈልጋል፣ ረጂ ተቋማም አብረውን ለመስራት ቃል ገብተዋል ያሉን በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ግርማ ማሞ (ዶ/ር) ናቸው።

በ3ቱ ሀገራት ፕሮጀክቱ ሲተገበር የመሬት አፈርና ሰብል መረጃ ማዕከል ማቋቋም፣ የሰው ሀይል አቅም ግንባታ እና የተገኘው መረጃ ገበሬው እንዲጠቀመው ለማድረግ ስልጠና መስጠት ከተከወኑ ጉዳዮች መካከል ናቸው ተብሏል።

በአውሮፓ ህብረት በዴቨሎፕመንት ስማርት ኢኖቬሽን ስር የሚገኘው የግብርና ምርምር ፕሮግራም (DeSIRA) ፣ በኔዘርላንድስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በISRIC በጋራ የገንዘብ ድጋፍ ነበር የመሬት፣ የአፈርና የሰብል መረጃ አገልግሎት ፕሮጀክት በሙከራ ደረጃ ሲተገበር የነበረው፡፡
በረከት አካሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s








