top of page

ጥር 29 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Feb 6
  • 2 min read

ሩሲያ እና ዩክሬይን የጦር ምርከኞች ልውውጥ አደረጉ፡፡


ሁለቱም አገሮች እያንዳንዳቸው 150 የጦር ምርኮኞችን እንደተረከቡ TRT ፅፏል፡፡


ከዩክሬይን የተለቀቁት ሩሲያውያን የጦር ምርኮኞች በቤላሩስ የህክምና እና ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ተብሏል፡፡


የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በልዋጭ የተለቀቁላቸው የጦር ምርኮኞች ወደ አገራቸው መግባታቸውን አረጋግጠዋል፡፡


በማህበራዊ ትስስር ገፃቸውም ምርኮኞቹ የተለቀቁበትን እለት መልካም ቀን ነው ብለውታል፡፡


ሩሲያ እና ዩክሬይን የምርኮኞች ልውውጥ ያደረጉት በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ አመቻችነት መሆኑ ታውቋል፡፡


ለልውውጡ መሳካት ሁለቱም አገሮች በየፊናቸው ለተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ምስጋና ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡


የዩጋንዳ ፖሊስ ከባንክ ማጭበርበር በተዘረፈ ገንዘብ ምክንያት ዘጠኝ የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ ሹሞችን አሰረ፡፡


ጉዳዩ የኮምፒዩተር መረጃ በማመሳቀል (ሐኪንግ) ከማዕከላዊ ባንክ ከተዘረፈ 62 ቢሊዮን የዩጋንዳ ሽልንግ ጋር የተያያዘ እንደሆነ TRT አፍሪካ ፅፏል፡፡


በኮምፒዩተር መረጃ ማመሳቀል ከባንኩ የተዘረፈው ገንዘብ የ17 ሚሊዮን ዶላር ያህል የምንዛሪ ግምት ያለው ነው ተብሏል፡፡


የገንዘብ ሚኒስቴ መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ሹሞች በፖሊስ ተይዘው የታሰሩት በዘረፋው እጃቸው አለበት ተብሎ እንደሆነ ታውቋል፡፡


ለጊዜው የተያዙት ሹሞች በስም አልተጠቀሱም፡፡


ፖሊስ ጉዳዩን እየመረመርኩት ነው ማለቱን መረጃው አስታውሷል፡፡



በናይጀርያ ዛምፋራ ግዛት በአንድ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ማደሪያ ላይ በደረሰ ቃጠሎ የ17 አዳጊ ወጣቶች ሕይወት ተቀጠፈ፡፡


ቃጠሎው የደረሰው ከትናንት በስቲያ ሌሊት ቢሆንም ወሬው የተሰማው ግን ትናንት ማምሻውን ነው፡፡


በቃጠሎው ሕይወታቸው ካለፈው ሌላ 17 ተማሪዎች ደግሞ አካላዊ ጉዳት ደረሶባቸዋል መባሉን አናዶሉ ፅፏል፡፡


ቃጠሎው የተቀሰቀሰው ተማሪዎቹ በእንቅልፍ ላይ በነበሩበት ወቅት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡


የቃጠሎው መንስኤ ምን እንደሆነ ለጊዜውም አልታወቀም፡፡


ምርመራው መቀጠሉን የአደጋ ተከላካይ መስሪያ ቤት ሹሞች ተናግረዋል፡፡


በአደጋው ወቅት በተማሪ ማዳሪያ ክፍሎች ውስጥ ከ100 በላይ ተማሪዎች እንደነበሩ መረጃው አስታውሷል፡፡



በኮንጎ ኪንሻሣ የM -23 አማጺ ቡድን ታጣቂዎች ተጨማሪ ከተማ መያዛቸው ነዋሪዎች እና የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች ተናገሩ፡፡


አማጺያኑ ከሳምንት በፊት በምስራቃዊ ኮንጎ ኪንሻሣ ትልቋ የሆነችውን የጎማ ከተማን መያዛቸው ሲነገር ሰንብቷል፡፡


ትናንት ደግሞ ከቡካቩ በ96 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን ኔኔ ቢንቱ የተሰኘችዋን ከተማ መያዛቸው ተሰምቷል፡፡


አማጺያኑ በሳምንቱ መጀመሪያ የተናጠል የተኩስ አቁም አድርገናል ብለው እንደነበር አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡


ኔኔ ቢንቱ በጎማ እና በቡካቩ መካከል የምትገኝ ነች ተብሏል፡፡


መንግስት አማጺያኑ የተኩስ አቁም አድርገናል ማለታቸውን ማጭበርበሪያ ነው ሲል ጠርቶታል፡፡


የኔነህ ከበደ

Commenti


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page