top of page

ጥር  15፣2016 - በ5 ዓመታት ከግማሽ ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ሀገራት የሥራ እድል አግኝተው ተጉዘዋል ተባለ

ባለፉት 5 ዓመታት ከግማሽ ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ሀገራት የሥራ እድል አግኝተው ተጉዘዋል ተባለ፡፡

 

ከአረብ ሀገራት በተጨማሪ በአውሮፓም ኢትዮጵያዊያን የስራ እድል ማግኘት በሚችሉበት መንገድ ዙሪያም አማራጩ እየታየ ነው ተብሏል፡፡

 

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በፍልሰት ረገድ የፋይናንስ እና የደህንነት ተቋማት ባላቸው ሚና ዙሪያ የሚመክር ዝግጅት አካሂዷል፡፡

 

በዝግጅቱ ላይ ሲነገር እንደሰማነው የውጪ ሀገራት የስራ ስምሪት እና ህገ-ወጥ ፍልሰትን መልክ ለማስያዝ በፖሊሲም በአሰራርም የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው፡፡

 

መደበኛ የሆነውን ፍልሰትን በህግም፣በአሰራርም የማሻሻል ስራው፤ ኢትዮጵያ በህጋዊ መንገድ ወደ ውጪ ከሚሄዱ ዜጎቿ በሬሚታንስ የምታገኘውን ገቢ እንድታሳድግ ጭምር የሚረዳት ነው ተብሏል፡፡

 

በዝግጅቱ ላይ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና የገንዘብ አጠባና ዝውውርን በመከላከል የፋይናንስ ተቋማትና የፋይናንስ ደህንነት ሚናው ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡

 

ሀገርና ዜጎች ከመደበኛው ፍልሰት ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም በተገቢው መንገድ ማግኘት አለባቸው ሲባልም ሰምተናል፡፡

 

ይህንንም ለማድረግ ያሉትን ችግሮች ለይቶና ተቀራርቦ መስራት ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

 

በዝግጅቱ ላይ ተለዋዋጭ የሆነ በብሔራዊ ባንክ በየጊዜው የሚወጣ አሰራርና ሌላውም ከውጪ በሬሚታንስ እንዲሁም በኢንቨስትመንት የሚገኘው ገቢ እየረበሸው እንደሆነ ተነስቷል፡፡

 

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ባለፉት አመታት የውጭ ሀገር የሰራተኞችን የስራ ስምሪት ለማሻሻል በተሰራው ስራ ባለፉት 5 አመታት ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል አግኝተዋል ተብሏል፡፡

 

በአውሮፓ ሀገራት ለኢትዮጵያዊያን ሊኖር በሚችል የስራ እድል ዙሪያም ለስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጥናት ተጠንቶ መቅረቡንና አማራጭም እየታየ እንደሆነ ሲነገር ሰምተናል፡፡

 

እስካሁን በሰራተኛ ስምሪት ዙሪያ ኢትዮጵያ ከሳውዲ አረቢያ ፣ ጆርዳን ፣ ኳታር ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስና በቅርቡ ከሊባኖስ ጋር ስምምነት ተፈራርማለች ተብሏል፡፡

 

 

ቴዎድሮስ ወርቁ

 


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

 

 

bottom of page