top of page

ግንቦት 6 2017 - ከ2 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ለገበያ ይቀርብ ከነበረው ወተት 60 በመቶው ውሀ ነበረ፤ አሁን ግን ውሃ መጨመሩ ቢቀጥልም መጠኑ መቀነሱን ጥናት አሳየ፡፡

  • sheger1021fm
  • 3 hours ago
  • 1 min read

ከ2 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ለገበያ ይቀርብ ከነበረው ወተት 60 በመቶው ውሀ ነበረ፤ አሁን ግን ውሃ መጨመሩ ቢቀጥልም መጠኑ መቀነሱን ጥናት አሳየ፡፡


ገበሬው ለሰብሳቢዎች ሲሸጥ ወተቱ ላይ ውሃ ይጨምራል፣ ሰብሳቢው ለፋብሪካው ሲያስረክብ ውሃ ይጨምራል ቀጥሎም ፉብሪካዎች እንዲሁ ውሃ እንደሚጨምሩ ተነግሯል።


ይህንን ባደረግኩት ጥናት ለማወቅ ችያለሁ ያለው የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ነው።


በሀገሪቱ በ2014 እና በ2015 ዓ.ም ለገበያ ይቀርብ ከነበረው ወተት በአማካይ 60 ከመቶው ውሃ እንደነበረ የተጠቀሰ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት እስከ 10 በመቶው ውሃ ነው ብሏል።


በህጉ መሰረት ወተት ላይ ምንም ውሃ መጨመር እንደማይቻል ይታወቃል፡፡

በተሰሩ የግንዛቤ እና የክትትል ስራዎች መጠኑን መቀነስ ቢቻልም አሁንም ዜሮ ደረጃ ማውረድ ያስፈልጋል ተብሏል።


ለገበያ በሚቀርብ የወተት ምርቶች ውሃ ከመጨመር ባለፈ ወተቱ ከሚታልበበት አንስቶ እስከ ተጠቃሚው እስኪደርስ የፅዳት ማነስ እና ከጥንቃቄ ጉድለት የሚበከልበት አጋጣሚ ብዙ እንደሆነ ጥናቱ አሳይቷል፡፡


ይህም በሰዎች ጤንነት ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ በወተት  ዙሪያ ጥናት እንዳደረገ የሚናገረው በኔዘርላንድስ መንግስት የሚደገፈው ኤስኤንቪ (SNV) የተሰኘ ድርጅት ጠቁሟል።


በሀገሪቱ በባለስልጣኑ ፍቃድ ያላቸው 25 የወተት ፋብሪካዎች ቢኖሩም በአሁን ሰዓት ስራ ላይ የሚገኙት 12ቱ ብቻ ናቸው ተብሏል።


የተቀሩት 13ቱ በሀገሪቱ በተከሰቱ የፀጥታ ችግሮችና በሌሎች ምክንያቶች ስራ ማቆማቸውንም ከኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ሰምተናል።


ማንያዘዋል ጌታሁን

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page