top of page

ግንቦት 6 2017 - ሕወሓት የእርምት እርምጃ ባለመውሰዱ ምክንያት ከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዙን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተናገረ።

  • sheger1021fm
  • 15 minutes ago
  • 1 min read

ሕወሓት የእርምት እርምጃ ባለመውሰዱ ምክንያት ከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዙን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተናገረ።


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) ከፖለቲካ ፓርቲነት መሠረዙን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ እንደተናገረው ከዚህ ቀደም ህ.ወ.ሓ.ት በአመፅ ድርጊት በመሣተፉ ምክንያት ከፖለቲካ ፓርቲነት መሠረዙ የሚታወስ ነው ብሏል።

ይሁንና የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተደረገ በኋላ የህ.ወ.ሓ.ት ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲሰረዝ የተላለፈው ውሣኔ እንዲነሣ ቦርዱን ሚያዝያ 13 እና ሚያዝያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም መጠየቁን ከመግለጫው ተመልክተናል።


ሆኖም ቦርዱ በዐመጻ ድርጊት በመሣተፉ ከፖለቲካ ፓርቲነት የተሠረዘ ፓርቲ ሕጋዊ ሰውነቱ ከተሠረዘ በኋላ ሕጋዊ ሰውነቱን ለመመለስ የሚያስችል ሕግ ስለሌለ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ መልስ ሰጥቷል።


የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባርን ለማሻሻል የወጣውን ዐዋጅ ተከትሎ ህ.ወ.ሓ.ት በልዩ ሁኔታ ፓርቲ ሆኖ ለመመዝገብ መቅረብ የሚገባቸውን ሠነዶች በማያያዝ ጥያቄ ማቅረብ ይታወሳል፡፡



በዚህም መሰረት ህ.ወ.ሓ.ትን አስመልክቶ የፍትሕ ሚኒስቴር በሕግ በተሰጠው ሥልጣን ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ መነሻ ህ.ወ.ሓ.ት ሕጋዊ ሰውነት የሚያገኝበትን ሕግ መሠረት በማድረግ ቦርዱ በማሻሻያ ዐዋጁ መሠረት ፓርቲውን በልዩ ሁኔታ መዝግቦ ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ሰጥቶታል።

ሆኖም ህውሓት ምዝገባውን ተከትሎ እንዲፈጽም የተሰጠውን ትዕዛዝ ባለማክበሩ ቦርዱ በተለያየ ጊዜ ማሳሰቢያ ቢሰጥም ፓርቲው ግን በሕግ የተጣለበትን ግዴታ እንዳልፈፀመ በመግለጫ ተነግሯል፡፡


በመሆኑም ቦርዱ የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የቦርዱ ውሣኔ ላይ ፓርቲው በሦስት ወር ዕግድ ጊዜ የዕርምት ዕርምጃ ሳይወስድ ቢቀር በዐዋጅ መሠረት ቦርዱ የተለየ አካሄድ ሳይከተል የፓርቲውን ምዝገባ እንዲሠርዝ ቦርዱ በወሠነው መሠረት ፓርቲው ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ከግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ከፖለቲካ ፓርቲነት የተሠረዘ መሆኑን ወሥኗል ብሏል።


ማርታ በቀለ

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page