ግንቦት 22 2017 - የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የታጣቂዎች በምክክር አለመሳተፋቸው እንደሚሳስበው ተናገረ፡፡
- sheger1021fm
- 1 day ago
- 1 min read


ኮሚሽኑ ይህን የተናገረው ዛሬ ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር ለ3 ቀናት የሚቆየውን አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ማካሄድ በጀመረበት ወቅት ነው፡፡
በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ ንግግር ያደረጉት የአገራዊ መክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕ/ሮ መስፍን ዓርዕያ የትግራይ ክልል በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፍ ማድረግ እና ከውጭ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያን አጀንዳዎችን ማሰባሰብ በአሁኑ ወቅት አጀንዳ ከማሰባስብ አኳያ የሚቀሩ ዋና ስራዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን በምክር ሂደት የተሳተፉ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም የተወሰኑት በየራሳቸው ምክንያት ያልተሳተፉ አሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
መሳሪያ አንግበው ጫካ የገቡ ታጣቂ እህት ወንድሞቻችንም የዚህ ታሪካዊ ሂደት አካል አለመሆናቸው ኮሚሽኑን እና ሌሎች ባለደርሻ አካላትን የሚያሳስብ ጉዳይ ነው ሲሉ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
መሳሪያ አንግበው እየተዋጉ ያሉ ወገኖችም ሆኑ እየተሳተፉ ያልሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ምክክሩ ይመጡ ዘንድ ዋና ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ካላቸው ተቀባይነት እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት አንጻር በጎ ሚና የሚኖራቸው የፍርድ ሂደት ላይ ያሉ እና ስደት ላይ ያሉ ወገኞቻችን ጉዳይም ቀላል ግምት የምንሰጠው አይደለም ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡
ዛሬ የጀመረው የምክክር በፌዴራል ደረጃ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት 14ኛ መድረኩ ነው ተብሏል፡፡
ዛሬ መካሄድ በጀመረው የፌደራል ባለድርሻ አካላት የምክከር ሂዲት ላይ እንደ መከላከያና ፌዴራል ፖሊስ ያሉ የጸጥታ አካላት፣ የሃይማኖትና የፖለቲካ ተቋማት መሪዎዎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና የክልል ፕሬዘዳንቶችን ጨምሮ በርካታ አካላት ተገኝተዋል፡፡
ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት አጀንዳ የመቅረጽ ሂደት መጀመሩን የተናገረ ሲሆን እስካሁን 1746 የጥቃቅን ቡድኖች የአጀንዳ ሰነዶችን እንደተሰናዱም አስረድቷል፡፡
በማለዳው መርሃ ግብር ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን ተሳታፊዎች ሚኒስቴር መ/ቤቶች ፣ ሌሎችም ተቋማትና ማህበራት በነፃነት አጀንዳዎቻቸውን ለኮሚሽኑ እንዲያስረክቡም ዋና ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
Comments