top of page

ግንቦት 23 2017 - በኢትዮጵያ በየዓመቱ 9,000 ሴቶች በወሊድ ወቅት በሚከሰት ፊስቱላ ይጠቃሉ ተባለ።

  • sheger1021fm
  • 22 hours ago
  • 2 min read

ከእነዚህ ውስጥ 1,500 የሚሆኑት ብቻ በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙት 9 የፊስቱላ ህከምና ተቋማት ህክምና ያገኛሉ ሲባል ሰምተናል፡፡


አንዲት የፌስቱላ ተጠቂን ከህክምና እስከ ስነልቦና ድጋፍ ለማድረግና ወደ መደበኛ ህይወቷ ለመመለስ ሁለት መቶ ሺህ ብር እንደሚጠይቅ ተነግሯል።


ወሬውን የሰማነው በወሊድ ወቅት የሚከሰት ፊስቱላ ተጎጂዎችን ለማገዝ  የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ዛሬ ሲካሄድ ተገኝተን ነው።


የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ የተባበሩት መንግስታት ስነ-ህዝብ ፈንድ (UNFPA) ከጤና ሚኒስቴር፣ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር  የተዘጋጀ ነው።


የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ ላይ  የጤና ሚኒስቴር ሚኒስት መቅደስ ዳባ(ዶ/ር)፣ አምባሳደሮች፣ የኩባንያ ሀላፊዎች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

 

በኢትዮጵያ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰት የእናቶች ሞትና ፊስቱላን የመሳሰሉ ከባድ የጤና እከሎችን በመቀነስ ረገድ እየተስተዋለ ያለው የህከምና ባለሞያዎች እጥረትና በሰለጠነ የጤና ባለሞያ እገዛ በተገቢው ሰዓት የወሊድ አገልግሎት አለማግኘት እንቅፋት እየሆኑ ይገኛሉ ተብሏል።


የህፃናት ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን የመሳሰሉ ጎጂ ድርጊቶች አባባሽ ምክንያት መሆናቸው ተጠቅሷል።


በወሊድ ወቅት የሚከሰት ፊስቱላ አንዲት ሴት ህይወት  ወደዚህ አለም በማምጣት ሂደት ውስጥ ሊገጥማት የሚችል የጤና ጉዳት ነው።


ችግሩ የሚከሰተው በሰለጠነ የጤና ባለሞያ እገዛ በተገቢው ሰአት የወሊድ አገልግሎት ካለማግኘት የተነሳ በሚፈጠር የተራዘመ ምጥ አማካኝነት ነው።

የችግሩ ተጠቂ የሆኑ ብዙ ሴቶች ሽንትና ሰገራ የመቆጣጠር ችግር፣ እንዲሁም ረጅም ጊዜ ለሚቆይ አካላዊ ስቃይ ከመዳረጋቸዉም በላይ ለእድሜ ልክ ስነ-ልቦናዊ ችግርና መገለል ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡


በወሊድ ወቅት የሚከሰት ፊስቱላን ሙሉ በሙሉ መከላከል ይቻላል ሲባልም ሰምተናል።


በኢትዮጵያ በወሊድ ወቅት የሚከሰት ፊስቱላን ከአምስት ዓመት በኋላ  ለማጥፋት ያለመ አገር አቀፍ ዘመቻ እተካሄደ እንደሆነ ተነግሯል።


የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ በወሊድ ወቅት የሚከሰት ፊስቱላን በተመለከተ አጋርነትን ለማጠናከርና እየተሰሩ ያሉ ወሳኝ ስራዎችን ለማገዝ እንደሚረዳ ታምኖበታል።


ከዝግጅቱ የሚገኝ ገቢ በወሊድ ወቅት በሚከሰት ፊስቱላ እና የማህፀን መውረድ ተጠቂ የሆኑ ሴቶችን የመለየትና ትራንስፖርት የማቅረብ ድጋፍን ጨምሮ ነፃ የቀዶ ህክምናና አጠቃላይ የድህረ ቀዶ ጥገና ከትትል አገልግሎት፤ የተሀድሶና ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ በማድረግ ተጠቂዎች ከማህበረሰባቸዉ ጋር ተመልሰው እንዲቀላቀሉ ድጋፍ ለማድረግ ይውላል ተብሏል።


የህይወት ክህሎትና የሞያ ስልጠና በመስጠት የተጠቂ ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ነፃነትና ዘለቄታዊ መቋቋምን ለማረጋገጥ ድጋፍ ማድረግ፤ እና በወሊድ ወቅት የሚከሰት ፊስቱላ እና የማህፀን መውረድ የመሳሰሉ የእናቶች ጤና ችግሮችን ለመከላከልና የማህበረሰብ ግንዛቤን ለማሳደግ እገዛ  ማድረግ ደግሞ ከገቢ ማሰባሰቢያ በሚገኝ ገንዘብ የሚሰሩ ስራዎች ናቸው ሲባል ሰምተናል።


ንጋቱ ሙሉ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page