top of page

ግንቦት 21 2017 - የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የስደት ምንጭ፣ የአካባቢ መራቆትና ግጭት ለስደት ያለውን ተፅእኖ የሚያጠና ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

  • sheger1021fm
  • 2 days ago
  • 2 min read

ዜጎቻቸው በብዛት ይሰደዱባቸዋል የተባሉ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የስደት ምንጭ፣የአካባቢ መራቆትና ግጭት ለስደት ያለውን ተፅእኖ የሚያጠና ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።


ፕሮጀክቱ ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ ገንዘብ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ የአካባቢ ጥበቃ ማዕከል እና ኔትዎርክ የሚሰራ ነው ተብሏል።


የአካባቢ መራቆት፣ የአየር ንብረት ለውጥና ግጭት በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ስደት እንዲጨምር ትልቁ ምክንያት ሆኗል ተብሏል።


ይህ የስደትን ምንጭ ያጠናል፣ በስምንት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ያለውን የፖሊሲ ማዕቀፍ ይፈትሻል የተባለው ፕሮጀክት ችግሩን ደረጃ፣ በመረጃ እና ጥናት ላይ ተመስርቶ በመመልከት ውጤቱን ማቅረብን ያለመ ነው።


ለ18 ወራት የሚቆየውንና ስምንት ሀገራትን ይመለከታል የተባለውን ፕሮጀክት ባለቤት ሆኖ የሚመራው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ የአካባቢ ጥበቃ ማዕከል እና ኔትዎርክ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር መኩሪያ አርጋው እንዳሉት ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል በተሰናዳ አህጉራዊ ጉባኤ ይፋ የሆነው ፕሮጀክት በመሬት ላይ ያለውን የ #ስደት ችግርና በየሀገራቱ ያለውን የፖሊሲ ማእቀፍ ለመመልከት የሚረዳ ነው።

‘’ሀገራት ይበጀኛል ያሉትን ፖሊሲ በየጊዜው ያወጣሉ፣ የኛ ዓይነት የጥናትና ምርምር ተቋም ደግሞ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ጥናትን በማድረግ ትክክለኛውን መረጃ መፈተሽና ለፖሊሲ ግብአት እንዲሆን የማቅረብ ሀላፊነት አለበት’’ ብለዋል።


ዛሬ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክትም ሲጠናቀቅ የአካባቢ መራቆትና ግጭት በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ምን ያክል የስደት ምክንያት እየሆነ እንደሆነ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውጤትን ይዞ የሚመጣ ነው ብለዋል።


በዚህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ጨምሮ በስምንት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ያለው ፖሊሲ ይፈተሻል፤ በየሀገራቱ ያለው የስደት ምንጭ በደንብ ይተነተናል፣ የአፍሪካ ህብረትና ኢጋድ የፖሊሲ ማዕቀፍንም በማየት የአካባቢውን የስደት ምንጭ በመረጃ ለማወቅ ይረዳል ብለዋል።


በዝግጅቱ ላይ ሲነገር እንደሰማነው የአካባቢ መራቆትና ግጭት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ዜጎች ስደት ትልቁ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ነው።


በአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ መራቆት ምክንያት የግብርና ምርት ይቀንሳል፣ የተፈጥሮ ሀብት ሽሚያው ደግሞ መልሶ የግጭትና ጦርነት ምክንያት ይሆናል ይህ ደግሞ ስደትን ያስከትላል ተብሏል።


የኢትዮጵያ የስደትና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን በአየር ንብረት ለውጥ፣ በግጭትና ሌሎችም ችግሮች ምክንያት ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ በሚሊየን የሚቆጠሩ ስደተኞች በኢትዮጵያ መጠለያዎች ውስጥ እንዳሉ ጠቅሰው ከዚህ ውስጥ 99 በመቶዎቹ የኢጋድ አባል ሀገራት ዜጎች ናቸው ብለዋል።


ከፍተኛ ቁጥር ያለው የስደተኛ ቁጥር መኖር መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማዳረስም ችግር እየሆነ ነው ብለዋል።


በስደተኛ ካምፖች ካሉ ስደተኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያውም ለሰዓታት ብቻ የሚያገኙት ሰባት በመቶው ብቻ ናቸው ብለዋል።


ከዘጠና በመቶ በላዩ የሀይል እና የማብሰያ ምንጫቸው የማገዶ እንጨት ነው ሲሉ ተናግረዋል።


በአካባቢው የስደትን ምንጭ በጥናት ማወቅና ችግሩን ለመቋቋምም በጋራ መስራት የግድ አስፈላጊ እንደሆነም አንስተዋል።


የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአካዴሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ጄይሉ ዑመር በዓለም ባንክ የተሰራውን ሪፖርት በመጥቀስ የአካባቢ መራቆትና ግጭት በአፍሪካ የስደት ምክንያት መሆኑ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስረድተዋል።


በመረጃው መሰረት የአካባቢ መራቆትና ግጭት በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ2050 በምስራቅ አፍሪካ ለአስር ሚሊየን ዜጎች ከቀዬአቸው መፈናቀልና ስደተኛ መሆን ምክንያት ይሆናል።


ፕሮጀክቱን የበላይ ሆኖ የሚመራውና የዛሬውን የማስጀመሪያ አህጉራዊ ጉባኤ ያሰናዳው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ የአካባቢ ጥበቃ ማዕከል እና ኔትዎርክ በአካባቢ ጥበቃና ሌሎችም ጉዳዮች መፍትሄ የሚያቀብሉ የምርምር ስራዎችን ለመስራት በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2006 የተመሰረተ ተቋም ነው።


ዛሬ በአፍሪካ ከ40 በላይ ድርጅቶች ማህበርተኛው ሆነዋል ተብሏል።


ቴዎድሮስ ወርቁ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Commentaires


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page