ግንቦት 19 2017 - ከስፔን መንግስት በተገኘ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የስነ ተዋልዶ ጤና ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
- sheger1021fm
- 2 days ago
- 2 min read
ከፈረንሳይ መንግስት በተገኘ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የስነ ተዋልዶ ጤና ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።
ፕሮጀክቱ የስነ ተዋልዶ ጤና ሽፋን ዝቅተኛ በሆነባቸው በተመረጡ የአፋርና ሶማሌ ክልል ወረዳዎች የሚተገበር ነው ተብሏል።
በስፓኒሽ ዴቭሎፕሜንት ኮርፖሬሽን የተደረገው የ700 ሺህ ዩሮ ወይም በወቅቱ የምንዛሬ ዋጋ ሲሰላ የ101.5 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ፕሮጀክቱ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በክልሎቹ የተጠቀሰው የቤተሰብ እቅድና የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት የሚሰጥበት እንደሆነ የነገሩን የስነ ተዋልዶ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ማህበራት ህብረት ዳይሬክተር አቶ አበበ ከበደ ናቸው፡፡
ፕሮግራሙ በክልሉ ያለውን ዝቅተኛ የቤተሰብ እቅድና የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሽፋን ያሳድገዋልም ብለውናል፡፡

የቤተሰብ እቅድና የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ስፋኑ በሶማሌ ክልል 14 በመቶ፣በአፋር ክልል ደግሞ 30 በመቶ መሆኑን የሚናገረው የጤና ሚኒስቴር ለዝቅተኛነቱ ዋንኛው ምክንያት ከእምነት ጋር በተያያዘ የቤተሰብ እቅድ እንዳይጠቀሙ ያደረገ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳለ ጠቅሷል፡፡
ይህም በክልሎቹ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና የህፃናት ጋብቻ እንዲበረክት ምክንያት ሆኗል ያሉን በጤና ሚኒስቴር የስነ ተዋልዶ ጤና፣ የአፍላ ወጣቶችና የቤተሰብ እቅድ ፕሮግራም ሃላፊ የሆኑት ዶክተር አለማየሁ ሁንዱማ አመለካከቱ እንዲስተካከል በስራዎቻችን የጎሳ መሪዎችንና የሃይማኖት አባቶችን እያሳተፍን ነው ብለውናል፡፡
ሲሰቴርሃዋ አብዱ በአፋር ክልል ጤና ቢሮ የእናቶችና ህፃናት ጤና ባለሙያ ናቸው እርሳቸው እንደሚሉት በክልላቸው የቤተሰብ እቅድን ላለመጠቀም ባህላችንና ሃማኖታችን አይፈቅድም የሚል የተሳሳተ አመለካከት አለ፤ ከአፋር ክልል ከ5 ዓመት በፊት የአገልግሎቱ ሽፋን ከ10 በመቶ ያልበለጠ ነበር አሁን 30 በመቶ ማድረስ ተችሏል፤
የህፃናት ጋብቻ አሁንም ድረስ በስፋት አለ፤የሴት ልጅ ግርዛት የሚፈፀመውም ከበድ ባለ መንገድ በመሆኑ ወደ ቤተሰብ እቅድ አገልግሎት መምጣት ለሴቶቹ ከባድ ሆኗል የሚሉት ባለሙያዋ እንደ ዛሬው አይነት ፕሮጀክቶች አጋዥ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአፋር ክልል አዋሽና አሚባራ ዞን፤ በሶማሌ ክልል ፋፈንና ሲቲ ዞኖች የሚተገበረው ፕሮጀክቱን ለመትግበራው ስኬታማነት 99 በመቶ ህዝቧ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነባትና ከፍተኛ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚ ያለባትን የኢንዶኒዢያን ልምድ ተወስዷል መባሉንም ሰምተናል፡፡
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://shorturl.at/21bFN
댓글