ግንቦት 13 2017 - በአዲስ አበባ በመንገድ ላይ በሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች የሚከሰት የእግረኞች የአካል ጉዳት ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል ተባለ፡፡
- sheger1021fm
- 7 minutes ago
- 1 min read
በከተማዋ ከሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች ከአምስቱ አራቱ በመንገድ ተጠቃሚ እግረኞች ላይ የሚደርስ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ይህንን ያለው አመታዊው የመንገድ ደህንነትን የሚያሳየውና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣንና ብሉምበርግ በጎ አድራጎት ኢኒሼቲቭ ፎር ግሎባል ሮድሴፍቲ ጋር በመተባበር የተሰናዳ አመታዊ የመንገድ ደህንነት ሪፖርት ነው፡፡
የአዲስ አበባ አመታዊ የመንገድ ደህንነት ሪፖርቱ በመንገድ ተጠቃሚዎች ላይ የሚደርስ ሞት ከአጠቃላይ የትራፊክ አደጋ ከሚመዘገቡ ሞቶች 86 በመቶውን ይሸፍናሉ ብሏል፡፡
78 በመቶ የሚሆነው የትራፊክ አደጋ ሞት የሚከሰተውም በወንዶች ላይ ነው ተብሏል፡፡
በመንገድ ላይ በሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች ከሚከሰተው ሞት አርባ አምስት በመቶ የሚሆነው በወጣትና መስራት እድሜ ውስጥ ባሉና እድሜያቸው ከ 20 እስከ 39 ባለው ዕድሜ ውስጥ ባሉ ዜጎች ላይ መሆኑን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡
የትራፊክ አደጋ የሚደጋገምባቸው እና ሞት በተደጋጋሚ የሚከሰትባቸውን ቦታዎች በመለየት ማሻሻያዎች ለማድረግ ሪፖርቱ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን መስብሰቡ ተነግሯል፡፡
በዚህም አሁንም 86 በመቶ በትራፊክ አደጋ ጉዳት የሚደርስባቸው እግረኞች መሆናቸውን ያሳያል የሚሉት የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ክበበው ሚደቅሳ ናቸው፡፡
ለአደጋው በተደጋጋሚ መከሰትም እንደ ሕዝብ ትራንስፖርት መስጫ ያሉ ተሽከርካሪዎች አብዛኛውን ድርሻ እንደሚወስዱ አቶ ክበበው ተናግረዋል፡፡
በ2016 ከደረሱ የትራፊክ አደጋዎች ውስጥ በወንዶች ላይ የተከሰተው ከፍተኛ እንደሆነና 67 በመቶ የሞትና የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡
ይህ ግኝትም በአዲስ አበባ ላለፉት 7 ዓመታት በተከታታይ የተመዘገበ ቁጥር እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝቅተኛ የተሽከርካሪ መጠንና አነስተኛ የመንገድ መሠረተ ልማት ቢኖራትም ከፍተኛ የሞትና የአካል ጉዳት መጠን እንደምታስተናግድ የዓለም የጤና ድርጅት የመንገድ ደህንነት ሁኔታ መረጃ ያሳያል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የአደርጋ ሪፖርት እንደሚጠቅሰው ደግሞ በኢትዮጵያ በየ ሁለት ሰዓቱ 1 ሰው ሲሞት በቀን 13 እና በአመት ደግሞ ከ4000 በላይ ሰዎች በመንገድ ትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ያጣሉ ብሏል፡፡
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://shorturl.at/21bFN