ግንቦት 12 2017 - የውጪ ሃገር ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀሰ ንብረት ባለቤት የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር እይታ ተመራ፡፡
- sheger1021fm
- 23 hours ago
- 2 min read
የውጪ ሃገር ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀሰ ንብረት ባለቤት የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር እይታ ተመራ፡፡
የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባው የውጪ ሃገር ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀሰ ንብረት ባለቤት የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል፡፡
በዚህም ወቅት አንድ የምክር ቤት አባል ረቂቅ አዋጁ በዚህ ጊዜ ለውይይት መቅረቡ ተገቢ አይደለም የሚል ትችት ሰንዝረዋል፤ የውጭ ሃገር ካፒታል ወደ ሃገር ቤት ለማምጣት ታስቦ የተሰናዳ ቢሆንም የቤት ዋጋ በእጅጉ በናረበት በዚህ ጊዜ የማህበረሰቡን የቤት ባለቤትነት አቅም ሊፈታተን ይችላል ብለዋል፡፡
የምክር ቤት አባሉ በቅኝ ግዛት ውስጥ የነበሩ ሃገራትን ተሞክሮ በመጥቀስ ነዋሪውን ከመሃል ሃገር በማፈናቀል በውጭ ዜጎች መተካትን እንዳያመጣ ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
አዋጁ መፅደግ ያለበት ወደፊት የሃገሬው ሰው የቤት ባለቤትነት ሲረጋገጥ ነው ባይ ናቸው፡፡
የረቂቅ አዋጁን አስፈላጊነት ያስረዱት የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የውጭ ሃገራት ዜጎች የቋሚ ንብረት ባለቤት ይሁኑ ሲባል የሃገሬውን ሰው የንብረት ባለቤትነት መብት በማያጣብብ መልኩ ህጋዊ አሰራርን ተከትሎ ነው ብለዋል፡፡
አዋጁ ያስፈለገው የውጭ ሃገራት ዜጎች እምነት ኖሯቸው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድግ እምነት እንዲኖራቸው ለማድረግ እንዲሁም በአጠቃላይ የውጭ ካፒታል ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑንም የመንግስት ዋና ተጠሪው አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ስንት ዓመት የኖረ የውጭ ሃገር ዜጋ ነው የቤት ባለቤት መሆን የሚችለው የሚለውም በግልፅ ቢቀመጥ በሚል ከምክር ቤት አባላት በጥያቄ ተነስቷል፤ በሌላ በኩል በረቂቅ አዋጁ ማንኛውም የውጭ ዜጋ በኢትዮጵያ በማናቸውም አንድ ጊዜ የሚኖረው የማይንቀሳቀስ ንብረት ከፍተኛ ቁጥር ከአምስት እንዳይበልጥ በሚል የተቀመጠው ገደብ በጠየቁ ቁጥር አስከ 5 ንብረት እንዲይዙ የሚያደርግ ስለሆነ ቢስተካከልም ተብሏል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ለበርካታ ዓመታት በውጭ ዜጎች ላይ ተጥሎ የኖረውን የመኖሪያ ቤት ባለቤትነት መብት ክልከላ የሚያስቀር ይሆናልም ተብሏል።
ይሁንና መሬት የሁሉም ቁሳዊ ሀብት እና ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኑሮ መሠረት እንደመሆኑ መጠን የውጭ ዜጎችን የንብረት ባለቤትነት መብት ቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ከዚህ በመነሳት የውጭ ዜጎች በዚህ የንብረት መብት ተጠቃሚ ለመሆን ለአንድ ‘የሊዝ ይዞታ’ ሙሉ ዋጋ እና የመኖሪያ ቤት ግንባታ ወይም ለቀጥታ ‘ግዢ’ አላማ የሚያውሉት አነስተኛ የገንዘብ መጠን አንድ መቶ ሀምሳ ሺህ የአሜሪካን ዶላር እንዲሆን በረቂቅ አዋጁ ደንግጓል፡፡
ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የስራ እድል በመፍጠር ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪን በከፍተኛ መጠን ያመጣል የተባለው አዋጁ የነዋሪውን የቤት ባለቤትነት መብት እንዳይገድብ አተገባበሩ ከጥንቃቄ ጋር ይሁን ሲሉም የምክር ቤት አባላት አሳስበዋል፡፡
ምክር ቤቱ አዛሬ ውሎ የውጪ ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀሰ ንብረት ባለቤት የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ረቂቅ አዋጁን ለከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም ለህግና ፍትህ ገዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በ3 ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ መርቷል።
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://shorturl.at/21bFN
Comments