የፌደራል ግብር ከፋዮች በኮቴ ክፍያ፣ ነጋዴዎች ደግሞ በግብር ሰብሳቢዎች ስነ ምግባር ጉድለት መማረራቸው በፓርላማው ተነገረ፡፡
- sheger1021fm
- 13 minutes ago
- 2 min read
ታህሳስ 3/2018
የፌደራል ግብር ከፋዮች በኮቴ ክፍያ፣ ነጋዴዎች ደግሞ በግብር ሰብሳቢዎች ስነ ምግባር ጉድለት መማረራቸው በፓርላማው ተነገረ፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር በበኩሉ የኬላ ጉዳይ ከፍተኛ አጀንዳ ሆኖ መቆየቱን፤ እስካሁን ግን መፈታት እንዳልተቻለ ተናግሯል፡፡
የኮቴ ክፍያና የገቢ ሰብሳቢ ሰራተኞች ስነ ምግባር ጉዳይ ለህዝብ ተወካዬዎች ምክር ቤት እና ሌሎች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረቡን የፕላን ፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተናግሮ፤ ለዚህም ማብራሪያ እንዲሰጠው የገቢዎች ሚኒስቴርን ጠይቋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ይህን የጠየቀው ዛሬ ታህሳስ 3 ቀን 2018 ዓ.ም የገቢዎችን ሚኒስቴርን የ4 ወራት የስራ ክንውን ሪፖርትን ባደመጠበት ወቅት ነው፡፡
የሪፖርቱን ማብቃት ተከትሎ የቋሚ ኮሚቴውን ሪፖርት በንባብ ያቀረቡት የገቢ ዘርፍ ንዑስ ሰብሳቢ አቶ ደበበ በክልሎች የማዘጋጃ ቤቶች ገቢ ስም ሀገር አቋራጭ ዋና ዋና መንገዶች ላይ የተቋቋሙ ኬላዎች ለንግድ ስርዓቱ እንቅፋት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ህገ ወጥ ኬላዎች፤ ግብር ከፋዬች ምርትና ግብዓት በሚያጓጉዙበት ወቅት የኮቴ ክፍያ እና ሌሎች ስያሜዎችን በመስጠት አንዳንድ ጊዜ ተሸከርካሪው በያዘው ምርት መጠን በማባዛት እንዲከፍሉ መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡
ይህም ለተደራራቢ ግብር ስለዳረጋቸው ቅሬታችውን ለምክር ቤቱ እና ለሚመለከታቸው አካለት ማቅረባቸውን አስታውሰው፤ ለምን ችግሩን መፍታት እንዳልተቻለ አቶ ደበበ ጠይቀዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ የኬላ ጉዳይ ከፍተኛ አጀንዳ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመው፤ አስካሁን ግን መፈታት እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡

የኮቴ ክፍያ የፌደራል ግብር ከፋዬችን ስራ እና ግብይት እንደሚረብሽ እንዲሁም ኢንቨስትመንትን እንደሚያቀጨጭ የተወያየንበት ጉዳይ ቢሆንም ችግሩን ማስቀረት አልተቻለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የጭነት ተሽከርካሪዎች ለሚያገኙት የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት በመነሻቸው እና መዳረሻቸው ላይ ብቻ እንዲከፍሉ ከስምምነት ቢደረስም ከህግ ውጭ በየከተሞች በጫኑበት ልክ እየተሰላ እንዲከፍሉ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡
የጉሙሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው ጉዳዩን የማያውቀው የስራ ሃላፊም ሆነ የመንግስት ተቋም እንደሌለ አስረድተው ችግሩን ለመፍታት ግን ፍላጎት የለም ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ሌላው ቋሚ ኮሚቴው ምላሽ የጠየቀበት ጉዳይ በገቢ ስብሳቢ ባለሙያዎች ስነ ምግባር ጉድለት መማረርን የተመለከተ ነው፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ከሰራተኛው የስነ ምግባር ጉድለት ጋር በተያያዘ በተለይም በኦዲት፣ በክትትል እና በቁጥጥር ምክንያት ከፍተኛ ምሬት ከነጋዴዎች እንደሚነሳ አስታውሶ ችግሩን ለመፍታት ምን እየተሰራ እንዳለ ጠይቋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር በበኩሉ የስራተኞችን የስነ ምግባር ጉድለት ሊያስቀር እና ችግሩንም ለማቅለል የሚረዳ አዲስ የኦዲት መመርያ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን ተናግሯል፡፡
በለፉት አራት ወራት ከ170 በላይ በለሙያዎች ላይ የስነ ምግባር እርምጃ እንደተወሰዳቸው የተናገሩት የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስተር አይናለም ንጉሴ ከዚህ ውስጥ 10ሩ ከስራ ተባረዋል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ ችግሩን ለማቃለል ከእጅ ንክኪ ነጻ የሆነ አሰራር መዘርጋት መጀመሩን አብራርተዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
Telegram : https://t.me/ShegerFMRadio102_1
Facebook፡ https://web.facebook.com/Sheger102.1








