የጥቅምት 8፣2017 - የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሀይብሪድ ዲዛይንስ (ራይድ ትራንስፖርት) አብረን እንስራ ተባባሉ
- sheger1021fm
- Oct 18, 2024
- 1 min read
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሀይብሪድ ዲዛይንስ (ራይድ ትራንስፖርት) አብረን እንስራ ተባባሉ፡፡
ይህንንም በፊርማቸው አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሀይብሪድ ዲዛይንስ (ራይድ ትራንስፖርት) አብረው ለመስራት ዛሬ የተፈራረሙት በሶስት ዋና ዋና ዘርፎች አብሮ ለመስራት ነው፡፡

የሀይብሪድ ዲዛይንስ (ራይድ ትራንስፖርት) ደንበኞች የንግድ ባንክ የዲጂታል የክፍያ አማራጮች ክፍያቸውን መፈፀም ማስቻል የስምምነቱ አንደኛው አካል ነው፡፡
ራይድ በሚያቀርባቸው የተለያዩ ዲጂታል መንገዶች ላይ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በጋራ ለመሥራት ሁለተኛው ሰምምነት ሲሆን ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ግዥ ባንኩ ብድር ማቅረብ ደግሞ ሶስተኛው ስምምነት መሆኑ ተነግሯል፡፡
ይህንን ስምምነት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወጋየሁ ገብረማሪያም አና የሀይብሪድ ዲዛይንስ (ራይድ ትራንስፖርት) የሽያጭ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ጌታቸው ፈርመውታል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ባንኩ ለራይድ አሽከርካሪዎች የኤሌክትሪክ መኪኖችን ግዥ ብድር አንደሚያቀርብም ተነገሯል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 በጀት ዓመት 135.4 ቢሊየን ብር ገቢ አግኝቻለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 1.17 ትሪሊየን ብር በላይ ሲሆን፤ የባንኩ ደንበኞች ቁጥር ደግሞ ከ45 ሚሊየን በላይ መሆኑን ተነግሯል፡፡
በዛሬው ዕለት ከባንኩ ጋር አብሮ ለመስራት የተፈራረመው ሀይብሪድ ዲዛይንስ (ራይድ ትራንስፖርት) ትራንስፖርት ፈላጊውንና አሽከርካሪውን በማገናኘት በዘርፉ ከቀዳሚዎቹ አንዱ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም 70,000 አሽከርካሪዎች አብረውኝ እየሰሩ ይገኛሉ ብሏል፡፡
ንጋቱ ሙሉ











Comments