የዳግማዊ ሚኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል የዲኢንኤ፣ የሥነ-ምረዛ እና የጥቃት ምርመራዎችን ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ተናገረ፡፡
- 3 hours ago
- 1 min read
ሐምሌ 8/2018
የዳግማዊ ሚኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል ከዚህ ቀደም ሲሰጣቸው ከነበሩ እንደ አስከሬን፣ የእድሜ እና የጉዳት ምርመራዎች በተጨማሪ፣ ሌሎች አዳዲስ አገልግሎቶችን በቅርቡ ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ተነገረ።
በፎረንሲክ ሕክምናና ሥነ-ምረዛ ክፍል ይሰጣሉ የተባሉት አገልግሎቶች የዲ.ኤን.ኤ (DNA)፣ የሥነ-ምረዛ እና የጥቃት ምርመራዎች መሆናቸው ታውቋል።
አገልግሎቱን ለመጀመር አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችና መሣሪያዎች የተሟሉ ሲሆን፣ ባለሙያዎችም ሥልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙ የፎረንሲክ ሕክምናና ሥነ-ምረዛ ክፍል ኃላፊ ዶክተር ወይንሸት ዘውዴ ነግረዉናል።
ይሁን እንጂ ኃላፊዋ አገልግሎቱ በይፋ የሚጀመርበትን ትክክለኛ ጊዜ ከመናገር ተቆጥበዋል።

በቅርቡ ሥራ ከሚጀምሩት አገልግሎቶች መካከል አንዱ የአባትና የልጅ ዘረ-መል (DNA) የመለየት ሥራ ነው። ከዚህ ቀደም ይህ ምርመራ ከአስከሬን ናሙና ተወስዶ ላቦራቶሪው በሌላ ሆስፒታል ይሠራ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ወይንሸት፤ አሁን ግን ሙሉ ምርመራውና የመለየት ሥራው በራሱ በሆስፒታሉ ባለሙያዎችና መሣሪያዎች በተሟላ ሁኔታ መሰጠት ይጀምራል ብለዋል።
አገልግሎቱን ለመስጠት ያግዛሉ ተብለው ተገዝተው የገቡት አዳዲስ መሣሪያዎች በጣም ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የታገዙ መሆናቸውን የጠቆሙት ደግሞ በዳግማዊ ምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል የሥነ-ምረዛ ባለሙያና የምርመራ ክፍል ኃላፊ አቶ ካሳሁን አደም ናቸው።
ይሁን እንጂ አገልግሎቱ በተሟላና በአግባቡ እንዲሰጥ ከተፈለገ፣ መሣሪያዎቹን በብቃት የሚረዱና የሚያንቀሳቅሱ በቂ የሠለጠ የሰው ኃይል ማፍራት እንደሚያስፈልግ አቶ ካሳሁን አሳስበዋል።
ብዙ ጊዜ በሆስፒታሉ የሚሰጠው የፎረንሲክ አገልግሎት የአስከሬን ምርመራ ብቻ ተደርጎ እንደሚታሰብ የጠቀሱት ዶክተር ወይንሸት፤ ነገር ግን በሕይወት ላሉ ሰዎችም ጭምር የተለያዩ ምርመራዎች እንደሚሰጡ አስረድተዋል።
በቅርቡ ይጀምራሉ ከተባሉት አገልግሎቶች መካከልም በሕይወት ላሉና በፍትሕ አካላት ለሚጠየቁ፣ በተለይም የሕፃናት የዕድሜ፣ የጥቃትና የጉዳት መጠንን ለመለየት የሚያስፈልጉ ምርመራዎች እንደሚካተቱባቸው አብራርተዋል።
የፎረንሲክ ምርመራዎች ለፍትሕ ሥርዓቱ መፋጠን ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸዉ ያሉት ኃላፊዎቹ፤ ይህ ሳይንሳዊ የምርመራ ዘርፍ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠውና በአግባቡ ሊሠራበት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ….
ገዛ ጌታሁን

