የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ የመጠባበቂያ ክምችት ከወራት በኋላ ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚጠጋ አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት IMF ተናገረ፡፡
- 3 hours ago
- 3 min read
ሐምሌ 8/2018
የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ የመጠባበቂያ ክምችት ከወራት በኋላ ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚጠጋ አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት IMF ተናገረ፡፡
ይህም ከሁለት ወራት በላይ የውጭ ሸመታዋን ለመከወን የሚያስችል ነው ብሏል፡፡
ኢትዮ ከተቋሙ ጋር የጀመረችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሲጠናቀቅ ለሶስት ወር ተኩል ሸመታ የሚበቃ መጠባበቂያ ክምችት እንዲኖራት ይጠበቃል ብሏል፡፡
ይሁንና ይህ ግብ እንዳይሳካ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ስጋቶች መኖራቸውንም IMF በስጋትነት አንስቷል፡፡
ተቋሙ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከተጀመረ ወዲህ አምስተኛው ዙር ግምገማ አካሂዶ ሙሉ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡
132 ገፅ በያዘው ሪፖርቱ አጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ሁኔታና ስለተረጋገጡበት ስጋቶች በስፋት ተንትኗል፡፡
እስካሁን ጠንካራ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም መኖሩንና የኢራኑ ጦርነት ግን እንቅፋት መፍጠሩን አንስቷል፡፡
ጦርነቱ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም ያስችል ዘንድም ለወደፊት ከሚለቀቀው ብድር የሚታሰብ 200 ሚሊዮን ዶላር ተክሎበት በ5ተኛው ዙር የIMF የተራዘመ ብድር 464 ሚሊዮን ዶላር እንዲለቀቅ ማፅደቁን IMF በሪፖርቱ ተናግሯል፡፡
በሌላ በኩል የብር የመግዛት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መሄዱና በወር በአንድ ነጥብ ሶስት በመቶ እየተዳከመ መሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
ነገር ግን የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ የመጠባበቂያ ክምችቷ እያደገ ነው ተብሏል፡፡
በተያዘው የፈረንጆቹ አመት 2026 ሲጠናቀቅ የመጠባበቂያ ክምችቱ ለሁለት ወር የውጭ ምንዛሬ ግብይት የሚበቃ 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ብሏል IMF፡፡
ከሁለት አመት በኋላ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ሲጠናቀቅ ደግሞ ለ3 ወር ተኩል የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ ክምችት እንዲኖር ይጠበቃል ሲል ተንብየዋል፡፡
ነገር ግን ይህ ከግብ እንዳይደርስ ሊያደርጉ የሚችሉ ስጋቶችም እንደተደቀኑ በሪፖርቱ አካቷል፡፡
የኢራኑን ጦርነት ተከትሎ በአለም አቀፍ ደረጃ ያሻቀበው የነዳጅ ዋጋ ሙሉ በሙሉ የተጣራ ነዳጅ ከውጭ ገዝታ በምታስገባው ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ጥላውን እንደሚያጠላ ጠቅሷል፡፡
ለተራዘመ ጊዜ በውድ ዋጋ ነዳጅ ገዝታ ማስገባቷ እና ወደ ውጭ የምትልከው ወርቅና ቡና ደግሞ በአንፃሩ አለም ገበያ ላይ ዋጋቸው መቀነሱ የመጠባበቂያ ክምችቷን ለማሳደግ የያዘችው እቅድ ላይ ጫና ማሳደሩ አይቀርም ተብሏል፡፡

የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ገበያ እንዲኖር የፖሊሲ ለውጦች ጭምር ተደርገው እየተሰሩ ሲሆን አሁን ግን በጥቁር ገበያውና በመደበኛው የውጭ ምንዛሬ ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት በታሰበው መጠን እየጠበበ እንዳልሆነ የIMF 5ተኛው ዙር ሪፖርት አሳይቷል፡፡
በመደበኛው የውጭ ምንዛሬ ገበያ እና በትይዩው መካከል የዋጋ ልዩነቱ ከ10 እስከ 20 በመቶ እየዋዠቀ ቀጥሏል ብሏል፡፡
ባለፈው ግንቦት ወር የዋጋ ልዩነቱ ወደ 11 በመቶ መቀነሱን በመጥቀስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እያካሄደ ያለው የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ልዩነቱ እንዲጠብ አስተዋጽኦ ካደረጉ እርምጃዎች መካከል ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል፡፡
ባለፉት 11 ወራትም 14 ጨረታዎችን በማካሄድ ማዕከላዊ ባንኩ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶለር ለባንኮች አከፋፍሏል ተብሏል፡፡
እንዲህ ያለው እርምጃም የባንኮችን የውጭ ምንዛሬ ክምችት እንዳሻሻለው የIMF ሪፖርት ያሳያል፡፡
እስካለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻም በባንኮች ያለው የውጭ ምንዛሬ ተቀማጭ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር መድረሱም ተገምቷል፡፡
ይህም ቢሆን ጥቁር ገበያው እንዲበረታ እያደረጉ ያሉ ችግሮች መኖራቸውንም የ IMF ሪፖርት ያስረዳል፡፡
የመደበኛውና የትይዩ ገበያው የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ልዩነት እንዲጠብ የተለያዩ የፖሊሲ ጣልቃ ገብነቶች እየተደረጉ ቢሆንም ጥረቱ እንዳይሳካ አድርገዋል ያላቸውን ስድስት የአሰራር ችግሮችን ዘርዝሯል፡፡
በህጋዊ መንገድ እለታዊ የንግድ ልውውጦችን ለማካሄድ የሚሆን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት አሁንም ገደቦች መኖራቸው አንደኛው ችግር ነው ተብሏል፡፡
ከባንኮች የውጭ ምንዛሬ ለመግዛት የኮሚሽንና ተያያዥ ወጭዎች እየተጠየቁ መሆኑም ሰዎች የጥቁር ገበያውን እንዲያማትሩ ማድረጉ ሌላኛው ችግር ሆኖ ተጠቅሷል፡፡
ባንኮች ምንዛሬ ሲሸጡ ከፍተኛ ትርፍ የሚስገኝላቸውን ግብይት መርጠዋል ያለው IMF ለሚሸጡት ዶላር 4 በመቶ ኮሚሽን እንደሚያስከፍሉ ብሔራዊ ባንክም 2 ነጥብ 5 በመቶ ኮሚሽን የሚቆርጥበት መሆኑን ጠቅሷል፡፡
በነገራችን ላይ ሰሞኑን የገንዘብ ፖሊስ ኮሚቴው ባሳለፈው ውሳኔ ብሔራዊ ባንክ የሚቆርጠውን ኮሚሽን ከ2 ነጥብ 5 በመቶ ወደ አንድ ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ አድርጓል፡፡
በተጨማሪም በመደበኛው ገበያ ውስጥ ከምንዛሬ መዋዠቅ ራስን ለመከላከል የሚያስችሉ የፋይናንስ መሳሪያዎች አለመኖራቸውም ገዥዎችን ወደ ትይዩ ገበያው ሊገፋቸው የሚችል አንዱ ምክንያት ሆኖ ተነስቷል፡፡
እንዲሁም ካፒታልን ወደ ውጭ ሃገር ለማውጣት ወይም በውጭ ኢንቨስት ለማድረግ የህግ ገደቦች በመኖራቸው ያንን ለማለፍም ሰዎች የጥቁር ገበያውን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡
የብሄራዊ ባንክ ለወርቅ ግዥ የሚከፍለው ተጨማሪ ማበረታቻ ከአለም አቀፍ ገበያ እስከ 15 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑ የትይዩ ገበያውን የምንዛሬ ተመን በመወሰን ረገድ የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለው IMF ስጋት በሚል ካስቀመጣቸው ዝርዝሮች መካከል ናቸው፡፡
እንዳጠቃላይ ግን እስካሁን የኢራኑ ጦርነት ያደረሰው ተፅዕኖ ቢኖርም ፣ የንግድ ሚዛን ጉድለቱ ከፍ ያለ ቢሆንም ኢኮኖሚው ይህን መቋቋም ችሏል ብሏል IMF በ5ተኛ ዙር የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ግምገማ ሪፖርቱ፡፡
የንግድ ሚዛን ጉድለቱም በሚጠናቀቀው 2026 አመት ፤ ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ይጠበቃ ሲል ተንብዩዋል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን





Comments