ኤም.ኤስ.አይ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር የሚተገብረው የቤተሰብ ዕቅድና ሥነ-ተዋልዶ ጤና ፕሮጀክት ባለፈው 1 ዓመት ለ750,000 በላይ ሰዎች አገልግሎት መስጠቱ ተነገረ።
- 31 minutes ago
- 1 min read
ሐምሌ 8/2018
ኤም.ኤስ.አይ (MSI) ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር የሚተገብረው የቤተሰብ ዕቅድና ሥነ-ተዋልዶ ጤና ፕሮጀክት ባለፈው 1 ዓመት ለ750,000 በላይ ሰዎች አገልግሎት መስጠቱ ተነገረ።
በጌትስ ፋውንዴሽን አንድ ቢሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ከአመት በፊት የተጀመረው የስነ-ተዋልዶ ጤና እና ቤተሰብ ዕቅድ ፕሮጀክት በአራት ክልሎች (በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሲዳማ እና በትግራይ ክልሎች) እየተተገበረ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ በተለይም በጦርነቱ ምክንያት ከአካባቢያቸው ለተፈናቀሉና የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት ባልቻሉባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ሰዎች የስነ ተዋልዶና የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ለመስጠት ያለመ መሆኑ ተጠቅሷል።
እስካሁን ከ750 ሺህ በላይ ሰዎች የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ አድርጓል፣ አጠቃላይ የቆይታው ጊዜም አራት አመት ነው ተብሏል።

በአማራና በትግራይ ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉና የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት ባልቻሉባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ሰዎች ፕሮጀክቱ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ሲሉ ኤም.ኤስ.አይ (MSI) ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶ/ር አበበ ሽብሩ ተናግረዋል ።
የጸጥታ ችግሮች እና የነዳጅ አቅርቦት እጥረቶች እንዲሁም ባህላዊና ሃይማኖታዊ ተጽዕኖዎች ፕሮጀክቱን ሲተገበር ያጋጠሙ ፈተናዎች መሆናቸው ተጠቅሷል።
በፕሮጀክቱ በ220 የጤና ተቋማት መተግበሩ፣ ለ849 የጤና ባለሙያዎች የክህሎት ስልጠና መሰጠቱ ተነግሯል።
በአጠቃላይ በመጀመሪያው አንድ ዓመት 31 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶች ለጤኖ ሚኒስቴር ተበርክተዋል።
ፕሮጀከቱ ሲጠናቀቅ 2.7 ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃማ ለማረግ ታስቧል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቅርቡ ይፋ በተደረገው የኢትዮጵያ የጤና እና ሥነ-ሕዝብ ጥናት (EDHS) መረጃ መሠረት፤ በአገሪቱ የዘመናዊ ቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚነት ደረጃ 34 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ይህንን ቁጥር ከአራት አመት ብኋላ 54 በመቶ ለማድረስ እየተሠራ እንደሚገኝ በጤና ሚኒስቴር የስነ-ተዋልዶ ጤና እና ቤተሰብ ዕቅድ፣ የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ፕሮግራም ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አለማየሁ ሁንዱማ ጠቁመዋል።
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ….
ምህረት ስዩም

