የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን ለማዘመንና ለማጠናከር ያለመ የ3 ቢሊዮን ብር የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክት ስምምነት ተፈረመ፡፡
- 1 hour ago
- 1 min read
ሰኔ 19/2018
የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን ለማዘመንና ለማጠናከር ያለመ የ3 ቢሊዮን ብር የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክት ስምምነት ተፈረመ፡፡

ፕሮጀክቱ በአምቦ ፣ ነቀምት እና አሶሳ ከተሞች አንደሚከናወን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከላከልን መግለጫ ላይ ተመልክተናል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስምምነቱ የተፈራረመው አልፋ (Alpha TND & LTD ) እና ካፒታል( Capital electech ) ከተሰኙ ኢንጂነሪንግ እና ዕቃ አቅራቢ ተቋማት ጋር ነው ተብሏል፡፡
የመልሶ ግንባታና የማሻሻያ ፕሮጀክቱ 325 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ ቮልቴጅ የኤሌክትሪክ መስመር የማሻሻያ ሥራዎች የሚከናወኑ ሲሆን፣ ይህም የኔትወርኩን አቅም ከማሳደግ ባለፈ የኃይል መቆራረጥ እና የቴክኒክ ችግሮችን ለመቀነስ እንደሚረዳ ተጠቁሟል ።
በተጨማሪም 235 ትራንስፎርመሮች ላይ የማሻሻያና የመልሶ ግንባታ ሥራ የሚከናወን ሲሆን ፣ ከእነዚህ 70 በአምቦ ፣ 121 በነቀምት እና 44 በአሶሳ እንደሚከናወን ተጠቅሷል፡፡
ፕሮጀክቱ ከአለም ባንክ በተገኘ 1.2 ቢሊዮን ብር እና 12 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ የሚተገበር ሲሆን፣ በአጠቃላይ ወጪው 3 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተነግሯል፡፡ በሁለት ዓመት ውስጥም ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) ‘‘ፕሮጀክቱ በከተሞቹ ያለውን የኤሌክትሪክ አቅርቦት አስተማማኝ በማድረግ ደንበኞች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያግዝ ፕሮጀክት " ነው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብና የጥራት ደረጃ መጠናቀቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ንጋቱ ሙሉ





Comments