የአዲስ አበባ ስነ ስሪት (የተዋቀረችበት መንገድ) ለከተማ ልማትና ዕድገት አስቸጋሪ አድርጓታል ተብሏል።
- 2 hours ago
- 2 min read
ግንቦት 4/2018
የአዲስ አበባ ስነ ስሪት (የተዋቀረችበት መንገድ) ለከተማ ልማትና ዕድገት አስቸጋሪ አድርጓታል ተብሏል።
አመሰራረቷም በተጠና የከተማ ፕላን ሳይሆን በልማዳዊ ሰፈራ መሆኑ ከነገስታቱ ጀምሮ ባለው ስርዓት ውስጥ አዲስ አበባን ለማዘመን ፈተና ሆኖ መቀጠሉም ተነግሯል።
ይህ የተነገረው ናሽናል ሚዲያ አክስዮን ማህበር "አዲሲቱ አዲስ" በሚል ርዕስ የአዲስ አበባ ከተማን የማደስና የልማት ሥራዎች፣ በጎ ዕድሎችና ፈተናዎች ላይ ያተኮረ ውይይት በተካሄደበት መድረክ ላይ ነው።

በመድረኩ ላይ የዳሰሳ ፅሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዳዊት በንቲ (ዶ/ር)፤ አዲስ አበባ ከሌሎች የዓለም ከተሞች በዕድሜ ትንሿ መሆኗን አንስተዋል።
ከተማዋ የተቆራረጠች እና ለዋና ከተማነት የማትመች ቦታ ላይ ነች ያሉት ዳዊት(ዶ/ር)፤ ይህም በየጊዜው ከተማዋን ለማልማት ጥረት ሲያደርጉ ለነበሩ አገዛዞች ፈተና ሆኖ መቀጠሉን አስረድተዋል።
በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት በእዮቤልዩ የሲመት በዓልና እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ላይ አዲስ አበባን ለማልማት እና ለማዘመን ጥረት መደረጉን፣ በደርግ እና የኢህዴግ ዘመንም ከተማዋን የማዘመን ሥራዎች ሲሰሩ እንደነበር ያስረዱት መምህር ዳዊት በንቲ ይሁን እንጂ ይህንን የሚያሳይ የከተማ ልማት ሙዚየም የለንም ብለዋል።
ይህም በቀደምት ስርዓቶች ከተማዋን ለማልማት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የነበሩ ጉድለቶችና በጎ ጎኖችን ለመገምገም አስቸጋሪ መሆኑን አስረድተዋል።

በመድረኩ ላይ የደሰሳ ፅሁፍ ያቀረቡት ሌለኛው ባለሞያ የከተማና ቀጠናዊ ፕላኒግ ረዳት ፕሮፌሰር እና ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት እሸትአየሁ ክንፉ (ዶ/ር) ናቸው።
እሸትአየሁ(ዶ/ር) አዲስ አበባ ወደፊት ምን ያህል የህዝብ ቁጥር መያዝ አለባት፣ ድንበሯን እስከምንድን ነው፣ የሀገር የኢኮኖሚ ማዕከልነቷ ይቀጥል ወይስ ሌላ መፍትሔ ይኑር፣ የሚሉ ጥያቄዎችን የሚመልስ ፖሊሲ መዘጋጀት አለበት የሚል ሃሳብ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማን የማደስና የልማት ሥራዎች፣ በጎ ዕድሎችና ፈተናዎች ላይ ባተኮረው ውይይት የዘርፉ ምሁራን፣ የሚዲያና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የአዲስአበባ ከተማና የፌደራል የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈውበታል።
በውይይቱም የኮሪደር ልማቱ ተስፋና ስጋት፣ የከተማ አኗኗር እና የሰዎችን ህይወት ስለ ማቅለል፣ የአዲስ አበባ የወደፊት የዕድገት ጉዞ እና ሌሎችም ሃሳቦች ላይ ውይይት ተደርጓል።
ንጋት መኮንን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7





Comments