top of page

ለመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መታወቂያ ለመስጠት የተጀመረው ስራ ከምን ደርሶ ይሆን?

  • 59 minutes ago
  • 2 min read

ግንቦት 4/2018

ለመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መታወቂያ ለመስጠት የተጀመረው ስራ ከምን ደርሶ ይሆን? የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤትን ጠይቀናል፡፡


የሚዲያ ባለሞያዎች የሙያ ማህበር የሆነው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሚዲያው ዘርፍ ያሉ ባለሞያዎችን መዝግቦ የሞያ ብቃት ማረጋገጫ መታወቂያ ለመስጠት የሚያስችለውን ጥናት ማድረጉን የተናገረው የዛሬ ዓመት በዚህ ወቅት ነበር፡፡


102 የሚደርሱ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትን በአባልነት እንደያዘ የሚናገረው ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ምን ያህል ጋዜጠኞች እንዳሉ ለማወቅ ከመመዝገብ ጀምሮ የሞያ ብቃት ማረጋገጫ መታወቂያ ለመስጠት እየተዘጋጀሁ ነው ማለቱን ተከትሎ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣንን ጨምሮ ከጋዜጠኞችም ምክር ቤቱ የብቃት ማረጋገጫውን መስጠት አይችልም የሚሉ ትችቶች ሲሰነዘሩበት ነበር፡፡



የካቲት30 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ስራው የህግ መሰረት የለውም፤ ጋዜጠኞችን የመመዝገብም ሆነ የሙያ ማረጋገጫ የመስጠት ሃላፊነት በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ አልተሰጠውም በሚል እውቅና እንደማይሰጠው አሳውቆ የነበረ መሆኑን በማስታወስ፤ ስራው ከምን ደረሰ? ያልናቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ታምራት ሃይሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ተነጋግረናል፤ እርሳቸውም ስራውን ተቀብለውት ከመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጋር እንድንሰራ አቅጣጫ ሰጥተዋል ብለውናል፡፡


የምክር ቤቱ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ታምራት ሃይሉ አዋጁ በሚዲያዎችና በጋዜጠኞች መካከል በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ፤ ሞያውን ሊያበረታ የሚችል የእርስ በእርስ ቁጥጥር ስርዓት እንዲኖር እውቅና የሚሰጥ በመሆኑ ነው ስራውን የጀመርነው፤ በዚህም አባል የሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ያሏቸውን የጋዜጠኛ ብዛትና የስራ ድርሻ፤ በዝርዝር እንዲሰጡን እየጠየቅን ነው፤ በሚሰጠን መረጃ ላይ ተመስርተን የሙያ ማረጋገጫውን(PRESS ID) እናዘጋጃለን በማለት ጠቀሚታውንም ያስዳሉ፡፡


በተጨማሪም ምክር ቤቱ በሞተኞች መካከል የሚኖርን የእርስ በርስ ቁጥጥር ስርዓት እየዘረጋ ነው የሚሉት አቶ ታምራት ጋዜጠኞችን የሚያስከስስ ነገር ካለ ባቋቋምነው የግልግል ዳኝነት እንድንመለከተው ይደረግ፤ በግልግል ዳኝነት ታይቶ ከዚያ ካለፈ ነው መከሰስ ያለበት ብለን እየሰራን ነው ሲሉም ይጠቅሳሉ፡፡


የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት እያዘጋጀሁ ነው ባለው የጋዜጠኞችንና የመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎችን በሚይዘው ዳታቤዝ ሁሉም የባለሙያው መረጃዎች ስለሚካተቱ የጋዜጠኛውን የስራ ላይ ደህንነት ያስጠብቃል፤ ችግር ሲገጥመው በቀላሉ ድምፅ እንድንሆነው ይረዳል ብሏል፡፡


የስራ ሃላፊው በዚህ ጊዜ እናደርገዋለን ብለው ቁርጥ ያለ ጊዜ ባያስቀምጡም መረጃዎችን የማሰባሰብ ስራውን እንዳጠናቀቅን የሞያ ማረጋገጫ መታወቂያውን የምክር ቤቱ አባል ለሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እንሰጣለን ብለዋል፡፡


ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ…

ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


YouTube : https://shorturl.at/18TS1

WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx

X :- https://x.com/shegerfm?s=2

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page