የንጹህ መጠጥ ውሃ ለማዳረስ ፈጠራ ላይ የተሰማሩ የግል ተቋማት የፋይናንስ አቅርቦት ላይ መሰራት አለበት ተባለ
- 2 hours ago
- 2 min read
ሚያዝያ 16/2018
የንጹህ መጠጥ ውሃና ከንጽህና አጠባበቅ ጋር የተያያዙ ስራዎችን በኢትዮጵያ ለማዳረስ ስራ ፈጠራ ላይ የተሰማሩ የግል ተቋማት የፋይናንስ አቅርቦት ላይ መሰራት አለበት ተባለ፡፡
የንጹህ መጠጥ ውሃና ንጽህና አጠባበቅ ወይም ሳኒቴሽን አገልግሎቶችን ማግኘት መብት ቢሆንም በኢትዮጵያ በብዙ ምክንያቶች ይህንን የሚያገኙት ካለው የህዝብ ቁጥር አኳያ ግን በቂ አይደሉም ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ከ10 ዓመታት በላይ በንጹህ መጠጥ ውሃና የሳኒቴሽን አገልግሎቱን በመደገፍ ሲሰራ የቆየው አኳ ፎር ኦል የተባለ አለምዓቀፍ ተቋም በዘርፉ የፋይናንስ ድጋፍ ከሚያቀርቡ ተቋማትና በግል በስራው ላይ ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር ባካሄደው ምክክር ላይ ነው ይህንን የሰማነው፡፡
በግል የንጹህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አቅርቦት ላይ አገልግሎቱን ለመስጠት የፋይናንስ ምንጭ ማግኘት ዋነኛ ችግር በመሆኑ እዚህ ላይ እየሰራን ሲሉ የአኳ ፎር ኦል ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ እዝቂኤል አይናለም ነግረውናል፡፡
በንጹህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎቶች ላይ ለሚሰማሩ የግል ተቋማት የፋይናንስ ድጋፍ የሚያቀርቡ እንደ ባንክና አነስተኛና መካከለኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ትርፉ ላይ ብቻ ከማትኮር በችግሩ ላይ በጋራ መስራት እንዳለባቸው አቶ እዝቂኤል ይናገራሉ፡፡
አቶ አበራ እንዳሻው በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሲኒየር ኤክስፐርትና የሚኒስትሩ አማካሪ ናቸው፤ እርሳቸው እንደሚሉት ደግሞ በአብዛኛው በመንግስትና በዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት ላይ ብቻ መርኩዞ የቆየውን የንጹህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ስራዎች ለመከወን የግሉ ዘርፍ እንዲገባበት የፖሊሲ ማሻሻያ ተደርጓል ይላሉ፡፡
በኢትዮጵያ በየዓመቱ ለንጹህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎቶች ፕሮግራም የሚያስፈልገው የፋይናንስ መጠን እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የሚጠቅሱት የአኳ ፎር ኦል ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ እዝቂኤል ይህንን ለመጋራት በግል ስራዎችን ለሚከውኑ ተቋማትና ግለሰቦች የብድርና ሌሎች የፋይናንስ አቅርቦቶች ሊመቻችላቸው ይገባል ብለዋል፡፡
ከንፁህ መጠጥ ውሃና የሳኒቴሽን አገልግሎት ጋር በተገናኘ በግል ተቋቁመው የፋይናንስ ድጋፍ ከሚደረግላቸው ውስጥ በመጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ የውሃ ማጣሪያ መሣሪያዎች አምራቾችና በግል መጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ የተሰማሩ ተቋማት ይገኙበታል ተብሏል፡፡
ምህረት ስዩም.....
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7

