የፍ/ቤትና የዐቃቤ ሕግ ውሳኔ እንዲከበርና የዘፈቀደ እስራት የሚፈጽሙ አካላት ተጠያቂነት እንዲሆኑ ኢሰመኮ አሳሰበ
- 1 hour ago
- 2 min read
ሰኔ 16/2018
የፍርድ ቤት እና የዐቃቤ ሕግ ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲከበር እና የዘፈቀደ እስራት የሚፈጽሙ አካላት ላይ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አሳሰበ፡፡
ኮሚሽኑ ይህን ያሳሰበው ዛሬ ሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ.ም የ11 ወራት አቅድ አፈጻጸሙን ሪፖርት ለህዘብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ባቀረበበት ሰነዱ ላይ ነው፡፡
የኮሚሽኑ የ2018 በጀት ዓመት የ11 ወራት ዋና ዋና የክንውንና የሀገራዊ የሰብአዊ መብቶችን ሪፖርት በ14 ገጽ አቅርቧል፡፡
የታሰሩ ሰዎችን መብት በተመለከተ ኢሰመኮ በ492 ፖሊስ ጣቢያዎች፣ 79 ማረሚያ ቤቶች እና 11 መደበኛ ያልሆኑ ማቆያ ሥፍራዎች ላይ ክትትል ማድረጉን በሪፖርቱ ጠቅሷል።

ኮሚሽኑ ክትትል ባደረገባቸው አማራ፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያና በአፋር ክልሎች ላይ “ወቅታዊ ጉዳይ”በሚል ሰበብ ታስረው የነበሩ 2,143 የሚሆኑ ሰዎችን ከእስር እንዲለቀቁ ማድረግ ችያለሁ ብሏል።
በተለያዩ ክልሎች በተጠርጣሪዎችና ታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ረገድ በርካታ ክፍተቶች አሉ ያለው ኮሚሽኑ ክትትል ባደረገባቸው ፖሊስ ጣቢያዎችና ማረሚያ ቤቶች ለተጠርጣሪዎች እና ለታራሚዎች ምግብ የማይቀርብ መሆኑ ማወቅ ችያለሁ ሲል አስረድቷል፡፡
ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተጠርጣሪዎችና ታራሚዎች ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረገ አገልግሎት በማቅረብ ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን ኮሚሽኑ አሳውቋል፡፡
ማረሚያ ቤቶች የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግና ጥራታቸውን በማስጠበቅ ረገድም ክፍተቶች መኖራቸውን ኮሚሽኑ አስረድቷል፡፡
በመሆኑም ኢሰመኮ የተጠርጣሪዎችንና የታራሚዎችን አያያዝና የሰብአዊ መብቶች ጥበቃን ለማሻሻል ተጣርጣሪዎች ሲታሰሩ ሰብአዊ መብቶችን ባከበረና በሕግ በተደነገገው አግባብና ሥርዓት ብቻ መሆኑን እንዳለበት አሳስቧል፡፡
የፍርድ ቤት እና የዐቃቤ ሕግ ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲከበር፣ ሕገ ወጥና የዘፈቀደ እስራት የፈጸሙ እና የፍርድ ቤት ውሳኔ የማይፈጽሙ አካላት ላይ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥም ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ጠይቋል፡፡
በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን መያዙ ለምርመራው የግድ አስፈላጊ ካልሆነ በቀር ሳያስሩ ምርመራው የሚከናወንበትን አሰራር እንዲዘረጋም የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በምከረ ሃሳቡ ጠቅሷል፡፡
ኢሰመኮ የይቅርታ እና አመክሮ ሕጎች በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበሩ በዛሬው የ11 ወር ሪፖርቱ አሳስቧል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i

