top of page

የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር በማድረግና በከባድ ሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ።

  • 51 minutes ago
  • 1 min read

ግንቦት 10/2018



የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር በማድረግና በከባድ ሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ።



የፌደራል ፖሊስ አፋልጉኝ ብሎ ማስታወቂያ ያወጣባቸውን 4 ተጠርጣሪዎች ፖሊስ ይዞ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።



የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት መዝገቡን ተቀብሎ ማየት የጀመረ ሲሆን፤ በዐቃቤ ህግ ክስ ላይ እንደተመላከተው ባለስልጣናቱ የፍቃድ አሰጣጥ መመሪያን በመጣስ ከተከሳሽ ወ/ሮ በረከት ወርቁ ጋር በመመሳጠር 466 ሺህ ሊትር ነጭ ናፍጣ ያለምንም ህጋዊ አሰራር እንድታገኝ አድርገዋል።



የእነዚህ ባለስልጣናት እና የግለሰቧ ህገ-ወጥ ድርጊት በመንግስት ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሱም በላይ በገበያው ላይ ለታየው የነዳጅ እጥረት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ክሱ ያስረዳል።



ጉዳዩን የያዘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት መዝገቡን ከፍቶ ተከሳሾችን የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።



ዛሬ በዋለው ችሎት የቀረቡ ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት የክስ መቃወሚያቸውን ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል።



ፍርድ ቤቱም ብይን ለመስጠት ለሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ/ም እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።



13 ተከሳሾች በቀረቡበት የክስ መዝገብ ላይ ያልተያዙት ማለትም ጌታቸው አሞኘ፣ በረከት ወርቁ (በረከት ገበሬዋ)፣ አቡሽ አየለ እና ይልቃል የኔሰው የተባሉት በፖሊስ ተይዘው እንዲቀርቡ፣ ካልቀረቡም ያልቀረቡበትን ምክንያት በፅሁፍ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ለፌደራል ፖሊስ ትዕዛዝ አስተላልፏል።



በተያያዘ ዜና በ"ፊንቴክ (Fintech) ኢንቨስትመንት ሽፋን በተፈጸመ መጠነ ሰፊ የማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ታዋቂ አርቲስቶች ዛሬ በነበራቸው ችሎት የክስ መቃወሚያ እንዲያቀርቡ ለሰኔ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።



በተጨማሪም ዐቃቢ ህግ የዋስትና መብቱን የተቃወመው መንሱር ጀማልም የዋስትና መብቱ ተከልክሎ በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 11 እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።



ገዛ ጌታሁን

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page