የነሐሴ 4 2018 የውጪ ሀገር ወሬዎች
- 1 day ago
- 2 min read
በሳውዲ አረቢያ ጂዛን በሚገኝ የነዳጅ ማጣሪያ ላይ ከባድ ቃጠሎ ተቅስቅሶ ነበር ተባለ፡፡
በጂዛኑ ማጣሪያ ላይ ቃጠሎ ተቅስቅሶ የነበረው ከባድ ፍንዳታ ከተሰማ በኋላ እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡
በጁቢየል የተፈጥሮ ጋዝ ማሰናጃ ከተማም ቃጠሎ ተቀስቅሶ ነበር ተብሏል፡፡
የሳውዲ ምንጮች ቃጠሎዎቹ ተቀስቅሰው እንደነበር ቢናገሩም ምክንያቶቹን በዝርዝር ከማስረዳት እንደተቆጠቡ ተጠቅሷል፡፡
ዩሮ ኒውስ እንደፃፈው ደግሞ የየመን ሁቲዎች በሳውዲዎቹ የነዳጅ አውታሮች ላይ የደረሰው ቃጠሎ የድብደባችን ውጤት ነው ብለዋል፡፡
የሳውዲ የኢነርጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስለ ሁቲዎቹ ድብደባ ባያነሳም በኢነርጂ አውታሮቹ ላይ ተቅስቅሶ የነበረው ቃጠሎ መጥፋቱን እወቁልኝ እንዳለ የፃፈው ደግሞ አሽራቅ አል አውሳት ነው፡፡
ሳውዲ አረቢያ እና ሁቲዎቹ ዳግም በጦር ወደመጠቃቃቱ እየተመለሱ መሆኑን መረጃው አስታውሷል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የጋዛን አለም አቀፍ ቦርድ የማረጋጊያ እቅድ ውድቅ ማድረጋቸው ተሰማ፡፡
ቀደም ሲል የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጋዛ ዘላቂ ሰላም ባቀረቡት እቅድ አለም አቀፉ ቦርድ መሰየሙ ይታወቃል፡፡
ቦርዱ በሰርጡ ቀጣይ የሰላም ውጥኖችን ስራ ላይ ለማዋል ባለ 15 ነጥቦች ፍኖተ ካርታ መንደፉን አልጀዚራ አስታውሷል፡፡
የፍልስጤማውያኑ የጦር እና የፖለቲካ ድርጅት ሐማስ እቅዱን ተቀብየዋለሁ በአፋጣኝም ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ ይዋልልን ብሏል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ግን እቅዱን ውድቅ ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡
ኔታንያሁ እቅዱን ውድቅ ያደረጉት በመጪው ጥቅምት ወር በእስራኤል በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ምክንያት እንደሆነ ተገምቷል፡፡
ኔታንያሁ የቦርዱን የሰላም እቅድ ውድቅ ማድረጋቸው የሀሳቡ ጠንሳሽ ከሆኑት ከአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ክፉኛ ሊያጋጫቸው እንደሚችል ተገምቷል፡፡
በጥቂት ወራት ውስጥ ከ178 ሺህ በላይ አፍሪካውያን ከደቡብ አፍሪካ ለቅቀው ወጥተዋል ተባለ፡፡
በደቡብ አፍሪካ ስደተኛ ጠሎቹ ወገኖች ሰነድ አልባ የውጭ አገር ሰዎች ተጠራርገው እንደወጡላቸው ግፊታቸው አበርትተውታል፡፡
በመንግስት ላይ በሰልፍ ጫና ከማበርታት አልፈው በአፍሪካውያኑ ስደተኞች ላይ እስር ግድያ የዘለቀ ጥቃት እያደረሱ ነው፡፡
በስደተኞች ጠሉ ጥቃት ህጋዊ የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ ያላቸውም ሰለባዎች እየሆኑ ነው ይባላል፡፡
በጥላቻ ጥቃት ስጋት በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን በጥቂት ወራት ጊዜ ለቅቀው እንደወጡ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
በአጭር ጊዜ ከደቡብ አፍሪካ ከወጡት መካከል 115 ሺህ ያህሉ የዚምባብዜ ዜጎች ናቸው፡፡
56 ሺህ ማላውያን ወደ እናት አገራቸው ተመልሰዋል፡፡
ናይጀሪያ ፣ ጋና ፣ ሞዛምቢክ እና ሌሶቶ እያንዳንዳቸው ከሺህ ያላነሱ ዜጎቻቸውን እና ተወላጆቻቸው የተቀበሉ አገሮች እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
_edited.jpg)



Comments