የቡና ምርትና ምርታማነትን በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ለማሳደግ ይረዳል የተባለ ሰነድ ለውይይት ቀረበ።
- 23 hours ago
- 1 min read
ሰኔ 20/2018
የቡና ምርትና ምርታማነትን በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ለማሳደግ ይረዳል የተባለ ሰነድ ለውይይት ቀረበ።
ውይይቱን ያዘጋጀው የግብርና ሚኒስቴር ከቡናና ሻይ ባለስልጣን ጋር በመሆን ነው።
ሀገር አቀፍ የቡና ልማት ፓኬጅ መተግበሪያ ሰነድ በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች፣ ባለሀብቶችና ተመራማሪዎች ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።
የግብርና ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ ኢትዮጵያ በሄክታር የምታገኘው ከ8 እስከ 9 ኩንታል ቡና ነው ያሉ ሲሆን ሌሎች ሀገራት በሄክታር የሚያገኙት 15 ኩንታል ነው ብለዋል።

ጥናት ተደርጎ በተዘጋጀው ሰነድ ይህን ቁጥር ወደ 21 ኩንታል ለማሳደግና ከዚህ የሚገኘው ገቢ ከ5 ዓመት በኋላ ወደ 6 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ መታቀዱን ጠቅሰዋል።
ይህን ለማድረግ በምርምር የተገኙ አዳዲስ የቡና ዝርያዎች መጠቀም ፣ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ እና የመስኖ ልማት በዚህ ዘርፍ መጠቀም መታቀዱንም ተናግረዋል።
የቡና ምርትን ማሳደግ መንግስት ሌላው የሰጠው ትኩረት መሆኑንም ተነስቷል።
ይህን እውን ለማድረግ የቡና እሴት መጨመር፣ ገበሬው ለዚህ ስራ ብቁ እንዲሆን ማድረግ የግብርና ሚኒስቴር በስፋት ለመስራት ማቀዱን ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከላከችው ቡና እስካሁን ድረስ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) አስረድተዋል።
በአለም ገብያ አንድ ቶን ቡና ባለፈው ዓመት ወደ 6,000 ዶላር ይሸጥ ነበር ያሉ ሲሆን ዘንድሮ የሚሸጥበት ዋጋ ከአምናው በ30 በመቶ በአለም ገበያ ቢወርድም ኢትዮጵያ በጥራት ላይ በሰራችው ስራ አንድ ቶን ቡና በ7,500 ዶላር ሲሸጥ ነበር ብለዋል።
በረከት አካሉ

