top of page

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ለስራ ጉብኝት አዲስ አበባ መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ይፋ አድርጓል።

  • 11 hours ago
  • 1 min read

ሰኔ 30/2018


የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ለስራ ጉብኝት አዲስ አበባ መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ይፋ አድርጓል።


ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳይ ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር መለሰ ዓለም አቀባበል ተደርጎላቸዋል።


የቱርኩ አናዶሉ እና የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት የሰርጌይ ላቭሮቭ የኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት የአፍሪካ ሀገራትን የመጎብኘት እቅዳቸው አካል እና መጀመሪያ ነው።

በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታም ዛሬ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጤሞቲዮስ እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ጋር ይመክራሉ ተብሏል።


በኢትዮጵያ የሚገነባው የኒውክሊየር ሀይል ማመንጫ ማዕከልን የተመለከተው ጉዳይ አንደኛው መነጋገሪያ ነጥብ ሊሆን ይችላል ብለዋል የመረጃ ምንጮቹ።


ካለፈው ዓመት የሁለቱ ሀገራት ንግግር የቀጠለ ያላቸውን የንግድ ግንኙነት የማሳደግ ሀሳብም ሌላኛው መነጋገሪያ ነጥብ ይሆናል ተብሏል።


በሩሲያ መንግስት በኩል የጉብኝቱ ዝርዝር ሀሳብ ይፋ አልተደረገም ያሉት የመረጃ ምንጮች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ላቭሮቭ ግን የመጀመሪያ መዳረሻቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ በኋላ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ይጓዛሉ ብለዋል።


የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከ4 ዓመት በፊት በተመሳሳይ ወደ ኢትዮጵያ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት መጥተው የነበረ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ ሀገራት መሀከል ያለው ግንኙነት የበለጠ ማደጉ ይነገራል።


ሩሲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና የኢንቨስትመንት እና ሌላውም ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ሲሆን ኢትዮጵያም ቀዳሚ አጋሮቼ ከምትላቸው ሀገሮች ውስጥ ነች።


ሩሲያ ከአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ጋር የምትመክርበት የአፍሪካ ሩሲያ ጉባኤን በየዓመቱ የምታሰናዳ ሲሆን ሶስተኛውን የአፍሪካ ሩሲያ ጉባኤ በሞስኮ በጥቅምት ወር ለማድረግ እየተሰናዳች መሆኑም ተነግሯል።

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page