top of page

የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአለም ዙሪያ ከኢነርጂ ደህንነትና ስብጥር ጋር የተገናኘ ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል።

  • 6 hours ago
  • 3 min read

ነሐሴ 12 2018


የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአለም ዙሪያ ከኢነርጂ ደህንነትና ስብጥር ጋር የተገናኘ ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል።


እንዲህ አይነት ጦርነት በተነሳ ቁጥር የተቀረው አለም የነዳጅ አቅርቦት የሚስተጓጎል ከሆነ አለም አስተማማኝ የኢነርጂ ምርጫዋ ምን ቢሆን ይበጃል? የሚል ነው ጥያቄው።


በሌላ በኩል ተፅዕኖው በደንብ ይታይ ከጀመረው የአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተገናኘም እንደ ነዳጅና የድንጋይ ከሰል ያለው አካባቢን በካይ የኃይል ምንጭ በምን ቢተካ ይበጃል? ተብሎም እየተጠየቀ ነው።


በብዙ ሀገሮች የቀጣዩ ዘመን አማራጭ የኃይል ምንጭ፣ከብክለትም ነፃ ተብሎ ግሪን ሃይድሮጂን (Green Hydrogen) መፍትሄ ተብሎ እየቀረበ ነው።


ግሪን ሃይድሮጂን ታዳሽና ንፁህ የሆነ እንደ ነፋስ፣ ፀሐይና ከውሃ ኃይል ማመንጫ የሚገኝ ኤሌክትሪክን በመጠቀም ከውሃ ውስጥ የሃይድሮጂንና የኦክስጅን ጋዝን ለብቻ በመለየት ንፁህ ሃይድሮጂንን ለኃይል ምንጭነት የመጠቀም ጥበብ ነው።


በዚህ መንገድ ግሬይ ሃይድሮጂን (Grey Hydrogen)፣ ብሉ ሃይድሮጂን (Blue Hydrogen) የተባሉት የሃይድሮጂን የኃይል ምንጮችም የሚመረቱ ሲሆን፣ የሚመረቱበት መንገድ ግን እንደ ድንጋይ ከሰል ያለውን በመጠቀም ስለሆነ በካይ ተብለው ይመደባሉ።


ግሪን ሃይድሮጂን ግን እንደ ነፋስና ፀሐይ ያለ ንፁህ የኃይል ምንጭን ስለሚጠቀም በአለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ ንፁህ የኃይል ምንጭ ተብሎ እየተጠቀሰ ነው።


ጥናቶች እንደሚያስረዱት በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 2025 የግሪን ሃይድሮጂን ገበያ በአለም ዙሪያ ወደ 2.79 ቢሊየን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ በ2032 ገበያው 74.81 ቢሊየን ዶላር ይደርሳል ተብሏል።


እንደነ ቻይናና ህንድ ያሉት ሀገሮች ንፁህና አስተማማኝ የኃይል ምንጭ የሚባለውን ግሪን ሃይድሮጂንን በመጠቀም ቀድመው ሄደዋል የሚሉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታው ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ፣ ኢትዮጵያም ወደዚህ አማራጭ መግባት የግድ ይላታል ብለዋል።


ይህንን የኃይል ምንጭ በጋዝ ወይም በፈሳሽ መልክ በማዘጋጀት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ተረጋገጧል።


በተለይ ከባቢያዊ አየርንም በመበከል ከፍተኛ ድርሻ ላላቸው ግዙፍ እንደ ነዳጅና የድንጋይ ከሰል ያለውን ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች ምትክ ሊሆን ይችላልም ተብሏል።


የኬሚካል አምራቾች፣ የብረት አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ የነዳጅ ማጣሪያዎች፣ መርከቦችና ግዙፍ አውሮፕላኖች እንዲሁም የጭነት ተሽከርካሪዎች ሁሉ እንቅስቃሴያቸውን በግሪን ሃይድሮጂን መተካት ይችላሉ ተብሏል።


የካርቦን ልቀትን በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 2050 ዜሮ ለማድረስ ላሰበችው አለም፣ አማራጭ መንገዷ ግሪን ሃይድሮጂን ሊሆን እንደሚችል የአለም የኢኮኖሚክ ፎረም መረጃ ያስረዳል።


የአለም የጤና ድርጅት የ2022 ሪፖርት ከአለም ህዝብ 99% ጤናማ ያልሆነና የተበከለ አየርን ስቦ ወደ ሰውነቱ እንደሚያስገባ፣ በዚህ ችግር ምክንያት በአለም ላይ በየዓመቱ ከ7 ሚሊየን በላይ ሰው እንደሚሞትና ከ90% በላይ ተጎጂዎች ደግሞ በዝቅተኛና መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ባሉ ሀገሮች የሚገኙ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።


ለዚህ ችግር ቀዳሚ መንስኤው ደግሞ አካባቢን በካይ በሆነ መንገድ የሚሰሩ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች፣ የትራንስፖርቱ ዘርፍና ሌላውም መሆኑን ዘርዝሯል።


በአለም አቀፍ ደረጃ ኤስቶኒያ ራሱን በራሱ የሚዘውርና በሃይድሮጂን ጋዝ የሚሰራ የከተማ አውቶቡስን በማስተዋወቅ በአለም ቀዳሚ ሀገር ሆናለች።


የግሪን ሃይድሮጂን ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች አካባቢን ካለ መበከላቸው በተጨማሪ የነዳጅ ፍጆታቸውም ከሌላው ተሽከርካሪ በ50% ያህል ያነሰ መሆኑ ይነገራል።


በአለም ዙሪያ በአንድ የሃይድሮጂን ሙሌት እስከ 2,400 ኪሎሜትር ድረስ መጓዝ የሚችሉ ተሽከርካሪዎች በሙከራ ደረጃ እየወጡ መሆኑም ይነገራል።


ለግዙፍ ኢንዱስትሪዎች፣ ለመርከብና አውሮፕላኖች እንዲሁም ለሌላውም ዘርፍ ነዳጅና ሌላውንም የኃይል ምንጭ ተክቶ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል እየተባለ ያለው ግሪን ሃይድሮጂንን ኢትዮጵያ እንዴት ልትጠቀምበት ትችላለች?


ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ:- "ኢትዮጵያ ያላት እምቅ የታዳሽ ኢነርጂ ምንጮችና በአጠቃላይ እምቅ ኢነርጂ አቅም በጣም ትልቅ ነው ይላሉ"።


"ኢትዮጵያ በቀላሉ ከአውሮፓ ጋር ትገናኛለች፣ለመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮችም ቅርብ ነች፣ከእስያ ሀገሮችም የሚያገናኝ ወሳኝ ቦታ ላይ የምንገኝ እንደመሆኗ በቀላሉ ግሪን ሀይድሮጂንን አምርተን መላክ እንችላለን" ብለዋል።


በአለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ ወይም በመህፃሩ IEA የ2026 ሪፖርት መሰረት ሙሉ ለሙሉ በታዳሽና ንፁህ የኃይል ምንጭ ላይ ጥገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ የግሪን ሃይድሮጂን በስፋት ለማምረት አቅም ካላቸው ሀገሮች ተርታ ነች ብሎ አስቀምጧታል።


ከፋይናንስና ከመሰረተ ልማት ጋር በተገናኘ ያለው ችግር ግን አፍሪካ እንደ አህጉር ለኢንቨስትመንቱ ተመራጭ እንዳትሆን ሊያደርጋት ይችላል ብሏል።


በሌላ በኩል አሁንም ከአፍሪካ ህዝብ 600 ሚሊየን የሚሆነው ኤሌክትሪክ ያላገኘ ስለሆነ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሀገሮቹ ቅድሚያ የሚሰጡት የኤሌክትሪክ ኃይልን ለዜጎቻቸው ለማዳረስ እንጂ የኤሌክትሪክ ኃይሉን ተጠቅመው ሃይድሮጂንን ለማምረት ላይሆን ይችላል ብሏል።


ስለዚህ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ሽፋን እቅዳቸውን ከግሪን ሃይድሮጂን ምርቱ ጋር ማጣጣፍ ይኖርባቸዋል ብሏል።


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ...



ቴዎድሮስ ወርቁ

Recent Posts

See All
የነሐሴ 12 የውጪ ሀገር ወሬዎች

#ሩሲያ የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ብሪታንያን በብርቱ አስጠነቀቋት፡፡ ፑቲን ብሪታንያ ለዩክሬይን ግዛት ተሻጋሪ ድሮኖችን ከማቀበል ብትቆጠቢ ይሻልሻል ማለታቸው ሬውተርስ ፅፏል፡፡ ቀደም ሲል ታይምስ ጋዜጣ ዩክሬይን በሩሲያ ላይ ግዛት ተሻጋሪ ጥቃት የምታደርሰው በብሪታንያ ስሪት ድሮኖች እንደሆነ መዘገቡ ተጠቅሷ

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page