በኢትዮጵያ በታክስና ግብር ስወራ፣ በሙስና፣ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በኦንላይን ማጭበርበር እና ከሌሎች ከባድ ወንጀሎች ጋር ግንኙነት አለው የተባለ በቢሊየን ብር የሚቆጠር ንብረት መታገዱን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።
- 6 hours ago
- 2 min read
ነሐሴ 12 2018
በኢትዮጵያ በታክስና ግብር ስወራ፣ በሙስና፣ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በኦንላይን ማጭበርበር እና ከሌሎች ከባድ ወንጀሎች ጋር ግንኙነት አለው የተባለ በቢሊየን ብር የሚቆጠር ንብረት መታገዱን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።

በ2018 ዓ.ም ብቻ በተከናወነ የምርመራና የሕግ ማስከበር ሥራ፣ በ544 የክስ መዝገቦች ሥር የተካተቱ በርካታ ሀብቶች ታግደው የሕግ ሂደታቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።
በዚህም መሠረት ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ፣ ዋጋቸው ከ220 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ አክሲዮኖች፣ ከ5 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ መሬት፣ ከ200 በላይ ቤቶች፣ ከ300 በላይ ተሽከርካሪዎች እና 69 ከባድ ማሽነሪዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉና እንዲታገዱ መደረጉን ሰምተናል።
ሥራ ላይ ከዋለ ከአንድ ዓመት በላይ የሆነው አዋጁ የሕገ-ወጥ ሀብት ምንጭን በጥብቅ በመመርመርና በማረጋገጥ፣ ንብረቱ ለመንግሥትና ለሕዝብ ጥቅም የሚወረስበትን ግልጽ ሕጋዊ አሰራር ዘርግቷል።
ሕጉ በጸደቀበት ወቅት እስከ 10 ዓመት ወደ ኋላ ተመልሶ ተጠያቂነት እንዲኖር መፍቀዱ በበርካቶች ዘንድ ከፍተኛ ክርክር አስነስቶ እንደነበር ይታወሳል።
በተለመደው የሕግ አሰራር አንድ ንብረት በሕገ-ወጥ መንገድ መገኘቱን ማስረዳት ያለበት ከሳሽ አካል ቢሆንም፤ በዚህ አዋጅ መሠረት ግን «ሀብቴ በሕጋዊ መንገድ የተገኘ ነው» ብሎ የማሳመንና የማስረዳት ሸክሙ ሙሉ በሙሉ የተከሳሹ ነው።
አዋጁ የታወቀ የገቢ ምንጭ ያላቸው ሰዎች ከሚያገኙት ገቢ ጋር ያልተመጣጠነና የተጋነነ የሀብት ልዩነት ሲገኝባቸው ወይም ምክንያታዊ ጥርጣሬ ሲኖር ምርመራ እንዲደረግባቸው ይደነግጋል።
በተመሳሳይ የታወቀ የገቢ ምንጭ የሌላቸው ግለሰቦች ያፈሩትን ሀብት እንዴትና በምን መንገድ እንዳጠራቀሙት ማስረዳት ካልቻሉ፣ ምርመራ ተካሂዶ ክስ በመመሥረት ንብረቱ እንዲወረስ ያዝል።
በጠቅላይ ዐቃቤ-ሕግ የሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ኃይሌ የአዋጁ ዋና ዓላማ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ሀብት መለየት፣ መመርመር፣ ማገድና የፍርድ ቤት ሂደቱ ሲጠናቀቅ ደግሞ ሙሉ በሙሉ መውረስ እንደሆነ አስረድተዋል።
በ2018 ዓ.ም የታገዱት ጥሬ ገንዘቦች፣ አክሲዮኖች፣ መሬቶችና ሌሎች ንብረቶች ከጀርባቸው ትላልቅ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ወንጀሎች ያሉባቸው እንደሆኑ የጠቆሙት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ የወንጀል ጉዳዮቹ በሕግ ሂደት ውሳኔ ሲያገኙ የውርስ አቤቱታው በይፋ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።
የሀብት ማስመለስ አዋጁ ትግበራ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል የተባለ ሲሆን፣ ሰሞኑንም የሀገሪቱን የፋይናንስ ሥርዓት የሚያናጉ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ 169 ግለሰቦች እንዲሁም በገቢዎችና ጉምሩክ ዘርፍ የተጠረጠሩ 109 ግለሰቦች ተለይተዋል።
ከእነዚህም መካከል እስካሁን 91 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ...
ገዛ ጌታሁን
_edited.jpg)


Comments