top of page

የህብረት ስራ ማህበራት ተጠያቂነት ያለበት አሰራር እንዲከተሉ ለማድረግ በተጀመረው የሪፎርም ስራ ባክኖ የነበረ 1.6 ቢሊየን ብር ማስመለስ ተችሏል ተባለ።

  • sheger1021fm
  • 2 hours ago
  • 1 min read

ጥር 22/2018

 

የህብረት ስራ ማህበራት ተጠያቂነት ያለበት አሰራር እንዲከተሉ ለማድረግ በተጀመረው የሪፎርም ስራ ባክኖ የነበረ 1.6 ቢሊየን ብር ማስመለስ ተችሏል ተባለ።

 

ሌሎችም በርካታ ውጤቶች በኀብረት ሥራ ማህበራት የሪፎርም ስራ መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሺሰማ ገብረሥላሴ ተናግረዋል።

 

ለአብነትም ማህበቱን በማዋሀድ፣ በማፍረስና ማጠናከር በተሰራው ስራ ከ120 ሺህ በላይ  የነበረው የኀብረት ሥራ ማህበራት ቁጥር አሁን ላይ ወደ 89 ሺህ ዝቅ ማለቱን ጠቅሰዋል።

 

የአመራር ስርአታቸውን ለማሻሻል በተሰራው ስራም ከ6900 መሰረታዊ ማህበራትና 57 ዩኒየኖች የአመራር ለውጥ አድርገዋል ያሉት አቶ ሺሰማ ወደ 4300 የሚሆኑ ሴቶችና ወጣቶች በአመራርነት እንዲካተቱ መደረጉንም ተናግረዋል።

አዳዲስ አባላትን በማፍራት የኀብረት ሥራ ማህበራት ዓመታዊ ካፒታል የማፍራት አፈፃፀማቸውን እንዲያሳድጉ እና  የቁጠባ መጠን እንዲጨምሩ ማድረግ መቻሉንም አመልክተዋል::

 

በከተሞች የምርት አቅርቦትና ግብይት ላይ በተሰራው ስራም በሀገር አቀፍ ደረጃ 378 ኀብረት ስራ ማህበራት ከ1400 በላይ በሚሆኑ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች ተሳትፈው ዋጋ እያረጋገጡ ይገኛሉ ብለዋል።

 

12ኛው የኅብረት ሥራ ማህበራት ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም ከጥር 26 እስከ 30 ቀን 2018  በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልና በአድዋ ድል መታሰቢያ እንደሚካሄድ ተነግሯል።

 

"ኅብረት ሥራ ከምርት እስከ ግብይት፤ ከአምራች እስከ ሸማች" በሚል መሪ ሃሳብ በሚዘጋጀው ኤግዚቢሽን እና ባዛር ላይ 360 የሚሆኑ የኅብረት ሥራ ማህበራት ይሳተፋሉ ተብሏል።

 

ማህበረሰቡ ለዕለት ተዕለት ፍጆታው የሚጠቀምባቸው ከ22 ሺህ ኩንታል በላይ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ይቀርቡበታል የተባለ ሲሆን ፤ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ቀጥታ ግብይት ይፈጸማል ተብሎ እንደሚጠበቅም ኮሚሽኑ የላከን መረጃ ያመለክታል።

 

ንጋቱ ረጋሳ

 

 

 

 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page