የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ፍትሃዊነትና አካታችነት የሚታዘቡ 10 ታዛቢዎችን እንደሚያሰማራ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ተናገረ።
- 4 hours ago
- 1 min read
ሐምሌ 2/2018
የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ፍትሃዊነትና አካታችነት የሚታዘቡ 10 ታዛቢዎችን እንደሚያሰማራ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ተናገረ።
የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሃምሌ 8 ለሚጀመረው ሃገራዊ የምክክር ጉባኤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት 10 ታዛቢዎችን እንዲያቀርብ ኮታ እንደሰጠው ምክር ቤቱ ነግሮናል።
ታዛቢዎቹ የምክክሩ ሂደት አካታችና ተደራሽ መሆን አለመሆኑን የሚከታተሉበት ሰነድ ተዘጋጅቶ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተረፈ ደጌቲ ነግረውናል።
ታዛቢዎቹ የተመረጡቱ የምክር ቤቱ አባል ከሆኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተረፈ፤ እነዚህ 50 የምር ቤቱ አባላት ዛሬ የተሰጠውን ስልጠና ወስደው ከመካከላቸው 10 ለታዛቢነት ይመረጣሉ ብለዋል።

በተዘጋጀው መከታተያ ሰነድ መሰረት ለሃገራዊ ምክክሩ የተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች የስብሰባ፣ የማደሪያ፣ የመመገቢያ፣ የመፀዳጃ ቦታዎች አመቺነት፤ በተለይ ለአካል ጉዳተኞችና ለህፃናት የሚሉ ጉዳዮች ታዛቢዎቹ ከሚከታተሏቸው መካከል መሆናቸውን ሰምተናል።
በተጨማሪም 4000 ውም የምክክሩ ተሳታፊዎች ከተሳትፎ በዘለለ ለመጨረሻው ምክረ ሃሳብ ምን ያህሉ ትርጉም ያለው ተሳትፎ አድርገዋል የሚለውም መካተቱን በምክር ቤቱ የአካታችነትና ተደራሽነት አማካሪ የሆኑት ዶክተር ታደሰ ገመዳ ነግረውናል።
በሃገራዊ ምክክሩ የሚመደቡት ታዛቢዎች ከምክክሩ አንድ ቀን ቀደም ብለው ቅድመ ዝግጅቱ ከመታዘብ ጀምሮ በየእለቱ ያለውን ሂደት እየታዘቡ ሪፖርት እንደሚያደርጉና በምክክሩ መጨረሻም የተጠቃለለ የታዛቢዎች ሪፖርት ለምክር ቤቱ እንደሚያቀርቡ ተጠቅሷል።
በየቀኑ የሚቀርበውን ሪፖርት መሰረት በማድረግ የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በሂደቱ ያሉ ክፍተቶችን ከስር ከስር እንዲያስተካክል የሚያግዘው መሆኑንም ሰምተናል።
ምንታምር ፀጋው

