top of page

ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጀው የኢሰመኮ የ5 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ

  • 4 hours ago
  • 2 min read

ሐምሌ 2/2018


የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን "የታጠቁ የጸጥታ አካላት መበራከት" ለትግበራው እንቅፋት ሊሆንበት እንደሚችል ስጋቱን ጠቅሶ ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጀውን የ5 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ይፋ አድርጓል፡፡


ኮሚሽኑ ከ2019 እስከ 2023 የሚያገለግለውን የ5 ዓመት የሰብአዊ መብት ስትራቴጂክ እቅድ ዛሬ ሐምሌ 2 ቀን 2018 ዓ.ም የተለያዩ አካላት በተገኙበት በዋና መስሪያ ቤቱ ይፋ አድርጓል።


የኢትዮጵያ ሰብብዊ መብቶች ኮሚሽን ዛሬ ይፋ ያደረገው እና ከትናንት ጀምሮ መተግበር የጀመረው እቅድ ከ7.6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ይህኛው የስትራቴጂክ እቅድ የተዘጋጀው በ2014 ጀምሮ እስከ 2018 ያገለገለውን እቅድ በማብቃቱ ነው።


በተጠናቀቀው ስትራቴጂ እቅድ ከ5,300 በላይ ለሚሆኑ አቤቱታዎች ምላሽ ተሰጥቷል።


ከ1,100 በላይ የመንግስት የስራ ሀላፊዎችን ተጠያቂ እንዳደረገ እና በህግ ወጥ መንገድ የታሰሩ ከ17,300 በላይ ሰዎችን እንዳስለቀቀ ኮሚሽኑ ተናግሯል፡፡


የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በወንጀልም ህግም ጭምር የተጠየቁ መሆናቸው የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሚዛኔ አባተ(ዶ/ር) ነግረውናል።

በተጨማሪም 2294 ተቋማት ላይ የሰብአዊ መብት ክትትል ተደርጓል።


የሚተገብረው ስትራቴጂክ ዕቅድ የተዘጋጀው በፍጥነት እየተለወጠ ላለው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ በሰነዱ ተጠቅሷል።


በውጤቶች ላይ ትኩረት ማድረግ፣ ለመከላከል ላይ ትኩረት መስጠት፣ ለተጠያቂነት፣ ለፍትህና ለትግበራ ትኩረት መስጠት ፣ ጠንካራ ተቋማዊ መሠረቶች መጣል እና ሌሎችም ጉዳዮች ደግሞ ከተጠቀሱት የአዲሱ ስትራቴጂ እቅድ መለያዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው።


የሰንዱ ይዘት በዝርዝር ያስረዱት ምክትል ኮሚሽነሩሚዛኔ አባተ (ዶ/ር) ስትራቴጂ እቅዱን ለመተግበር ሕገ-ወጥ የሲቪል ሰዎች ግድያና የአካል ጉዳት፣ የዘፈቀደ እና የተራዘመ እስር፣ አስገድዶ መሰወርና ጠለፋ ፣ ወሲባዊ ጥቃትን ጨምሮ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲሁም የታጠቁና የጸጥታ አካላት መበራከት ለትግበራው እንቅፋት ለሆኑ እንደሚችሉ አስረድተዋል ።


ማሰቃየት፣ ኢ-ሰብአዊ አያያዝና ሌሎች ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና የጦርነት ስጋቶች ፣ ቀጣይነት ያለው የተጠያቂነት ጉድለት እና አጥፊዎች ለፈጸሙት ጥሰት ሳይቀጡ የመቅረት ሁኔታ ፣ በነጻ ሚዲያና በጋዜጠኞች ላይ እየጨመረ የመጣ ገደብ የምግብ ዋስትና ማጣት እና ሌሎች ጉዳዮች እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል።


በአጠቃላይ ግጭት፣ መፈናቀል፣ የተጠያቂነት ተግዳሮቶች፣ የቴክኖሎጂ ለውጥ፣ ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ ጫናዎችና የማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ እኩልነት መጓደሎች በዚህኛው ስትራቴጂ እቅድም ሊቀጥሉ የሚችሉበት ሁኔታ ሰፊ ነው ይላል ሰነዱ፡፡


በሂደት ላይ ያሉ የለውጥና ማሻሻያ ጥረቶች፣ የብሔራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች፣ እያደገ የመጣው የሕዝብ የሰብአዊ መብቶች አረዳዶች ደግሞ ለእቅዱ ተግበራ አጋዥ ሊሆኑ ይችላል ተብሏል፡፡


እቅዱን ስራ ላይ ለማዋል 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ያለው ሰነዱ ከዚህ የገንዘብ መጠን ውስጥ 4.4 ቢሊዮን ብር ከመንግስት ለማግኘት ታቅዷል።


ቀሪውን 3.21 ቢሊዮን ብሩን ደግሞ ከተለያዩ ለጋሽ አካላት ለማግኘት መታሰቡ ተነግሯል።


ኢሰመኮ ዋና ሕገ መንግሥታዊና ሕጋዊ ተልዕኮውን ለመወጣት አስፈላጊ የሆነውን በቂ ሀብት መንግሥት እንዲመድብ መወትወቱን እንደሚቀጥል አሳውቋል፡፡


በዚህም ለመጀመሪያ አመት 1.1 ቢሊዮን፣ ለሁለተኛ ዓመት 1.3 ቢሊዮን ብር፣ ለሶስተኛው 1.5 ቢሊዮን ፣ ለአራተኛው 1.7 ቢሊዮን ብር ፣ ለአምስተኛው 1.97 ቢሊዮን በአጠቃላይ እቅዱን ለመተግብር 7.6 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ተብሏል።


ያሬድ እንዳሻው

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page