top of page

ወደ አውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የሚላክ ቡና ደን ሳይመነጠር የተመረተ እንደሆነ አረጋግጦ የመላክ ስራ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጀመራል ተባለ።

  • sheger1021fm
  • 2 hours ago
  • 1 min read

ጥር 22/2018

 

ወደ አውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የሚላክ ቡና ደን ሳይመነጠር የተመረተ እንደሆነ አረጋግጦ የመላክ ስራ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጀመራል ተባለ።

 

ህብረቱ ወደ አባል ሀገራቱ የሚላክ የግብርና ምርት ከደን ምንጣሮ ነፃ መሆን እንዳለበት የሚያስገድደውን ህግ ከአንድ ዓመት በኋላ ስራ ላይ ማዋል እንደሚጀምር ማሳወቁ ይታወሳል።

 

የአውሮፓ ህብረት በተለይ በታዳጊ ሀገራት የተመረቱ ዘጠኝ የግብርና ምርቶች ወደ አባል ሀገራቱ መግባት የሚችሉት፤ ከደን ምንጣሮ ነፃ በሆነ መሬት ላይ ተዘርተው የበቀሉ ከሆነ እና ለዚህም ማረጋገጫ ሲያቀርቡ ብቻ እንደሚሆን በመጥቀስ ይህንኑ የተመለከተ የሚል ህግ አውጥቷል።

 

በዚህ ክልከላ ውስጥ ከተካተቱ የግብርና ምርቶች ኢትዮጵያን የሚመለከተቱት ቡና እና አኩሪ አተር መሆናቸውን ሠምተናል።

 

ህጉ ከባለፈው ወር አንስቶ ስራ ላይ ይውላል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ተግባራዊ የሚሆንበት ጊዜ በአንድ ዓመት ተራዝሟል።

 

ኢትዮጵያም በተሰጠው አንድ ዓመት ጊዜ ወደ ህብረቱ የምትልከው ቡና ደን ሳይመነጠር የተመረተ እንደሆነ እያረጋገጠች ምስክር ወረቀት ለማዘጋጀት እየሰራች እንደምትገኝ ተጠቅሷል።

 

 አሁን ላይ እያንዳንዱ የቡና እርሻ መሬት ወደ መረጃ ቋት እየገባ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ቡና ፤ ሻይ እና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ፤ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የልማት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ተጋይ ኑሩ ነግረውናል።

 

በኢትዮጵያ ከሚመረተው ቡና ከ90 በመቶ በላዩ ከአርሶ አደሮች የሚገኝ እንደሆነ አቶ ታጋይ ተናግረዋል።

 

 አርሶ አደሮቹ ቡናውን የሚያመረቱበት መሬት ስፋት እጅግ አነስተኛ እና የተበጣጠሰ በመሆኑ የመረጃ ማሰባሰቡን ስራ ከባድ ያደርገዋል ብለዋል።

 

የተራዘመውን የአንድ ዓመት ጊዜ በመጠቀም ግን የሁሉንም አርሶ አደሮች መሬት ወደ መረጃ ቋት በማስገባት ቡናቸው ደን ሳይመነጠር የተመረተ እንደሆነ የሚያረጋግጠውን የምስክር ወረቀት መስጠት እንደሚጀመር ነግረውናል።

 

የአውሮፓ ህብረት ያወጣው ህግ የቡና አመራረት ከህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ነፃ ሊሆን ይገባዋል የሚል ድንጋጌንም ያካተተ እንደሆነ ተነግሯል።


ይህንንም የማረጋገጥ ማስረጃ ለማቅረብ የኢትዮጵያ ቡና ፤ ሻይ እና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር እየሰራሁ ነው ብሏል።

 

ሙሉ ዘገባውን ያድም….

 

ንጋቱ ረጋሳ

 

 

 

 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page