እድሜያቸው ከ14 እስከ 24 የሆኑ አፍላ ወጣቶች በተለይም ሴቶች ላይ እየታየ ያለው የኤች አይ ቪኤድስ ስርጭት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱን፣ ይህም ከፍተኛ ትኩረትእንደሚያስፈልገው ኔፕ ፕላስ (NEP+) የተባለ ድርጅት ተናገረ።
- 3 hours ago
- 2 min read
ሐምሌ 23 2018
እድሜያቸው ከ14 እስከ 24 የሆኑ አፍላ ወጣቶች በተለይም ሴቶች ላይ እየታየ ያለው የኤች አይ ቪኤድስ ስርጭት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱን፣ ይህም ከፍተኛ ትኩረትእንደሚያስፈልገው ኔፕ ፕላስ (NEP+) የተባለ ድርጅት ተናገረ።
Network of Networks of HIV Positives in Ethiopia ወይም ኔፕ ፕላስ ይህንን ያለው ከወር በኋላ የሚያካሂደውን ጠቅላላ ጉባኤውን በማስመልከት ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጥ ነው።
የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት መጠን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከአንድ በመቶ በታች ቢሆንም፤ እንደ አዲስ አበባ፣ ጋምቤላ፣ ትግራይ፣ አማራ ባሉ ክልሎች ዋና ዋና ከተሞች ስርጭቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ድርጅቱ ጠቅሷል።
በተለይ ደግሞ እድሜያቸው ከ14 እስከ 24 ያሉት ወጣቶች፣ ከዚህም ውስጥ ሴቶች ለቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጋለጡ መሆኑን የኔፕ ፕላስ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ታደሰ አስረድተዋል።
"በከተሞች የኤች አይ ቪ/ኤድስ ከፍተኛ የስርጭት (prevalence rate) እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ።
እነዚህ መረጃዎች ደግሞ የሩቅ ጊዜ መረጃዎች ሳይሆኑ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች መሆናቸውን በዚሁ አጋጣሚ መግለጽ እፈልጋለሁ፤ የቅርብ ጊዜ ዳታዎች ናቸው።
''አሁን ለምሳሌ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ብትሄዱ፣ ከዛኛው በር ጫፍ እስከዚህኛው በር ጫፍ የተደረደረ መኪና ልነግራችሁ አልችልም ወጣቶችን የሚፈልግ'' ''በፎቶግራፍ፣ በደላላ፣ በምን... የሚፈለጉ ናቸው ወጣቶቹ።
ከጫፍ እስከ ጫፍ መናኸሪያ ነው የሚመስለው እሄዳችሁ ብታዩ፤ በጣም የሚገርም ነው። ከጀርባው ደግሞ የዳንስ ቤት፣ አንዳንዴ ኢንጆይ (enjoy) የሚያደርጉበት፣ ወጣቶች ኢንጆይ የሚያደርጉበት የተለያየ ሩም (room) ያለበት ነው። ስለዚህ ለሴክስ ተጋላጭ ናቸው፡፡ ባለሀብቶች ናቸው እዛ ጋር የሚመጡት፣ ከተለያዩ ሴቶች ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ እሱን እንደ አንድ ምሳሌ ነው የነገርኳችሁ። ወጣቶቹ ላይ ካልሰራን ወጣቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተያዙ ነው" ብለዋል፡፡
ስለ ኤችአይቪ/ኤድስ በየሚዲያውና በየመድረኩ ይደረግ የነበረው የግንዛቤ ስራ ከዓለም አቀፍ ረጂ አካላት ይገኝ የነበረው ድጋፍ መቀዛቀዝ ጋር ተያይዞ መቅረት፣ የበሽታው ስርጭት በተለይ በአፍላ ወጣቶች ዘንድ ከፍ እንዲል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አቶ ካሳሁን አስረድተዋል።
በአሁኑ ሰዓት የፀረ-ኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒት አቅርቦት ምንም ችግር የለውም ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ ነገር ግን የኮንዶም አቅርቦት ችግር እንዲሁም የዋጋ መጨመር ችግር እንዳለ፣ ይህም ለወጣቶች ተጋላጭ መሆን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
"ኮንዶም ችግር አለ። መንግስት ኮንዶም ችግር የለም ይላል፤ በተግባር ስናየው ግን ኮንዶም ችግር አለ። በማንኛውም ጤና ተቋም ይገኝ ነበረ፤ አሁን ብትሄዱ አታገኙም። ስለዚህ ኮንዶሙ የት ነው ያለው? ፋርማሲ ነው። ስንት ነው የሚሸጠው? ልጆቹ መግዛት በሚችሉት ወጋ አይደለም፡፡ ኮንዶም መጠየቅ፣ ፋርማሲ ሄዶ መጠየቅ ራሱ እኮ በኢትዮጵያ ሁኔታ እኮ እንደ ሀፍረት ነው አይደል የሚቆጠረው? ማነው አሁን 'ኮንዶም ስጠኝ' ብሎ በፊታችሁ የሚጠይቀው? ያውም ብሩን ከፍሎ ፣ ብዙ ሰዎች ስለ ኤችአይቪ ጉዳያቸው አይደለም።
አሁን ጉዳያቸው ሴቷም ራሷ ብትሆን ስለ እርግዝና ነው እንጂ የምትፈራው፣ ስለ ኤችአይቪ ብዙ አታስብም። እርጉዝ ብሆን ብላ ነው የምትጨነቀው እንጂ ስለ ኤችአይቪ ጉዳይ አይደለም። ሲሉ አቶ ካሳሁን አስረድተዋል፡፡
ከተመሰረተ 20 ዓመት የሞላው ኔፕ ፕላስ፣ ኤችአይቪ/ኤድስ በደማቸው በሚገኝ ሰዎች የተመሰረቱ ከ500 በላይ ማህበራትንና 13 የማህበራት ጥምረቶችን የያዘ ድርጅት ነው።
ድርጅቱ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ላይ የሚደርስን መገለልን ለማስቆም፣ ሰርተው እንዲኖሩና መብታቸው እንዲከበር ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሷል።
በ20 ዓመታት ከዚህ ስራችሁ ምን የሚጨበጥ ውጤት አስግኝታችኋል ያልናቸው ዋና ስራ አስፈፃሚው የሚከተለውን መልሰዋል።
"በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን የታግንበት አመታት ናቸው፡፡
ትዳራቸውን የፈቱትን አስታርቀናል፣ የተበተኑ ልጆችን ሰብስበናል፣ የሞቱትን ቀብረናል፣ የታመሙትን አሳክመናል፤ ስለዚህ እነዚህ እነዚህን አግልግሎቶች በመስራት ነው የብዙ ሰዎችን ህይወት የታደግነው።
አርአያ ሆነናል፣ አስተምረናል፣ በመጽሔት፣ በቪዲዮ ሰዎችን በጣም አነቃቅተናል። የብዙ ሰዎች ቤት የፈረሰውን እንደገና ገንብተናል። ስለዚህ ይሄ ከምንሰጣቸው ሰርቪሶች መካከል አንዱ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ብዙዎችን ወጣቶች ደግሞ መታደግ እንፈልጋለን አሁን።"ኔፕ ፕላስ ከወር ግድም በኋላ 21ኛ ጉባኤውን እንደሚያደርግ አስረድቷል።
በዚህም በተለይ ኤችአይቪ/ኤድስን በሚመለከት እየተቀዛቀዙ የመጡ ስራዎችና መዘናጋቶች ትኩረት እንዲሰጣቸው ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግሯል።
ንጋቱ ሙሉ
_edited.jpg)


Comments