top of page

ኢትዮጵያ የትንባሆ ኢንዱስትሪዎች የሚያደርሱትን ተፅዕኖ በመቋቋም ከዓለም 6ኛ መሆኗን ሪፖርት አሳየ፡፡

  • 5 hours ago
  • 2 min read

ሐምሌ 10/2018


ኢትዮጵያ የትንባሆ ኢንዱስትሪዎች የሚያደርሱትን ተፅዕኖ በመቋቋም ከዓለም 6ኛ ከአፍሪካ 2ኛ መሆኗን አለም አቀፉ የትንባሆ ተፅዕኖ ተጋላጭነት ሪፖርት አሳየ፡፡


ለዚህም ምክንያቱ ጠንካራ የትንባሆ ቁጥጥር ህግ ያላት መሆኑና ኢንዱስትሪዎቹ ጫና እንዳያደርጉ መቆጣጠር በመቻሏ ነውም ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ በ2011ዓ.ም ባወጣችው የምግብና መድሃኒት አስተዳደር አዋጅ የትንባሆ ኢንዱስትሪን ጣልቃ ገብነት ስለመቆጣጠር በሰፈረው ድንጋጌ የትንባሆ ኢንዱስትሪዎች ከመንግስት አካላት ጋር ምንም አይነት የጥቅም ትስስር እንዳይኖራቸው ይከለክላል፡፡


እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ለመንግስት አካላት በስጦታ ገንዘብ እንዳይሰጡ፤ የበጎ አድራጎት ስራ ላይ እንዳሰማሩ አዋጁ ይከለክላል፡፡


ይህም የሆነበት ምክንያት በድጋፍ ስም የትንባሆ ምርት እንዳያስተዋውቁ፤ ስማቸውን እንዳይገነቡ፤ የትንባሆ ቁጥጥር ስራው ላይም ተፅዕኗቸውን እንዳያሳርፉ ነው፡፡



ይህንን መሰሉ ጣልቃ ገብነት በየሃገሩ መኖር አለመኖሩ ጂ.ጂ.ቲ.ሲ በተባለ አለም አቀፍ ተቋም በየአመቱ ይጠናል፤ የጥናቱን ውጤት መሰረት በማድረግ የሃገራት የትንባሆ ኢንዱስትሪዎች ጣልቃ ገብነት ደረጃ ይወጣል ያሉን ጥናቱን ከከወኑት መካከል የሆኑት አቶ አክሊሉ ጌትነት ናቸው፡፡


በጥናቱ የኢትዮጵያ የትንባሆ ኢንዱስትሪዎች ጣልቃ ገብነት መቀነሱ ታይቷል፤ ይህንን ጥናት መሰረት በማድረግ በወጣው አለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ 2ኛ ከአለም 6ኛ ሆናለች ብለውናል፡፡


አቶ አክሊሉ የጥናቱን ሂደት ሲያስረዱ አንዱ አለም አቀፍ መለኪያ ሃገሪቱ ጠንካራ የትንባሆ ቁጥጥር ህግ አላት ወይ? የሚለው እንደሆነና በዚህ በኩል ኢትዮጵያ ጠንካራ ህግ ያላት መሆኑን ጠቁመዋል፤

በተጨማሪም በሃገሪቱ ያለው የትንባሆ ኢንዱስትሪ የመንግስት አካላት የሚያደርጉትን የትንባሆ ቁጥጥር ስራ በገንዘብ ለመደገፍ መሞከር፤ ማህበራዊ ሃላፊነትን ለመወጣት በሚል ህጉን በመጣስ እገዛ አድርጓል ወይ? የሚሉና መሰል መመዘኛዎች በጥናቱ መካተታቸውንም ይሃገራሉ፡፡


የትንባሆ ኢንዱስትሪው በህግ ከተፈቀደለት ወጪ በሃዋሳ ከተማ ለማህበረሰቡ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ማስገንባቱን በመረጃ አሰባሰብ ወቅት ማግኘታቸውንና ተቆጣጣሪው የመንግስት አካል ወዲያውኑ አዳራሹን ከአገልግሎት በማገድ እርምጃ መውሰዱ የመከላከል ስራው ጠንካራ መሆኑን ያየንበት ነው ሲሉም አቶ አክሊሉ አጎናፍር አስረድተውናል፡፡


የዘርፉ ተቆጣጣሪ የሆነው የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የመድኃኒት ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ስዩም ወልዴ ውጤታማ በትንባሆ ቁጥጥር በአለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት መሸለሟ ጣልቃ ገብነቱን ጭምር መቆጣጠር በመቻላችን ነው ሲሉ ከትንባሆ ነፃ ቀን በተከበረበት እለት ተናግረው ነበር፡፡


በጥናቱ የትንባሆ ኢንዱስትሪዎች ጣልቃ ገብነት መጠን ከ0 እስከ 5 ደረጃ ላይ ያለ እንደሆነ ዝቅተኛ ሲሆን የኢትጵያ ደረጃ 2 መሆኑ እየቀነሰ መምጣቱን ማሳያ ነው፤ በአለም አቀፍ ደረጃ በመቶኛ በተቀመጠው የ2025 የተጋላጭነት ሪፖርትም ኢትዮጵያ 35 በመቶ አምጥታለች ተብሏል።


እ.ኤአ. በ2023 የነበራት ውጤት 37 ከመቶ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡


ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ….


ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…



YouTube : https://shorturl.at/18TS1








Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page