ከ3,800 በላይ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ አዘዋውረዋል የተባሉት እነ ይትባረክ ዳዊት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጣቸው፡፡
- 3 hours ago
- 1 min read
ሐምሌ 10/2018
ከ3,800 በላይ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ አዘዋውረዋል የተባሉት እነ ይትባረክ ዳዊት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጣቸው፡፡
ከ3,800 በላይ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ በማደራጀትና በማዘዋወር፣ ለ133 ሰዎች ሞት እንዲሁም ለ116 ሴቶች መደፈር ምክንያት ሆነዋል በሚል ክስ የተመሠረተባቸው እነ ይትባረክ ዳዊት ላይ ፍርድ ቤት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በአጠቃላይ 16 ክሶች የቀረቡባቸው 11 ተከሳሾች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ መካከል ስድስቱ በቁጥጥር ስር ውለው የዋስትና መብታቸው በመታገዱ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።
ቀሪዎቹ 5 ተከሳሾች ግን በሌሉበት ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በችሎቱ እየታየ ነው።
በዐቃቤ ሕግ ከቀረቡት 16 ክሶች መካከል ከኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ እስከ ሱዳንና ሊቢያ የሚዘልቅ ዓለም አቀፍ የወንጀል ቡድን በማደራጀት በበላይነት መምራት፤ ተጎጂዎችን "ወደ አውሮፓ በመሻገር የተሻለ ሥራ ታገኛላችሁ" በማለት በማሳመንና በማጓጓዝ፣ በመተማ በኩል አሻግረው፤ ሱዳንና ሊቢያ በሚገኙ መጋዘኖች ውስጥ በማሰር ከፍተኛ ስቃይ ማድረስ፣ ተጎጂዎች ሲሰቃዩ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን (ቪዲዮዎችን) ለቤተሰቦቻቸው በመላክ፣ ከእያንዳንዳቸው ከ750 ሺህ እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ በከባድ የስነ-ልቦና ጫና ማስገደድ የሚሉት በዋናነት ተጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ከ2015 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ከ3,800 በላይ ተበዳዮችን በማገት፣ ከቤተሰቦቻቸው ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሰበሰቡ በዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ላይ ተዘርዝሯል።
ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት በተከሳሽ ጠበቆች ለቀረበው የክስ መቃወሚያ ዐቃቤ ሕግ በጽሑፍ መልስ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ በዚሁ መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ለዛሬ ሐምሌ 10/2018 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ብይን ለመስጠት እንደገና ለሐምሌ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ገዛ ጌታሁን
_edited.jpg)
