ኢትዮጵያ ተወዳጁ ቡናዋ በአለም አቀፍ ደረጃ ይበልጥ ተመራጭ እንዲሆን፣ ይሰራል የተባለ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ማህበር ተመሰረተ።
- sheger1021fm
- 51 minutes ago
- 2 min read
ህዳር 17 2018
ኢትዮጵያ ተወዳጁ ቡናዋ በአለም አቀፍ ደረጃ ይበልጥ ተመራጭ እንዲሆን፣ የሚገኘው ገቢም እንዲያድግ ይሰራል የተባለ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ማህበር ተመሰረተ።
ማህበሩ በትናንትናው ዕለት የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ(ዶ/ር)፣ ቡና ላኪዎች በተገኙበት ይፋ ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ማህበር የኢትዮጵያን ቡና በአለም አቀፍ ደረጃ ያስተዋውቃል፣ የጥራት ደረጃው የጠበቀ እንዲሆን ይሰራል እንዲሁም ለቡና አምራቾች፣ ላኪዎች፣ ከቡና ጋር በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ግኑኝነት ላለቸው አካላት እድሎችን ይፈጥራል ተብሏል።

ማህበሩ ባለ ልዩ ጣዕም ቡና የሚባለው ቡና የትኛው ነው የሚለውን ከአምራቹ፣ ከላኪውና ከሌሎች ጋር በመሆን ይበይናል ሲሉ የማህበሩ ፕሬዚዳንት አሸናፊ አርጋው ነግረውናል፡፡
ባለ ልዩ ጣዕም ቡና ያልሆነው ነው እየተባለ የኢትዮጵያ ቡና ስም እንዳይጎድፍ እንሰራለን ሲሉም ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ማህበር ከዚህ ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ የልዩ ጣዕም ቡና ውድድር አንደሚያካሂድ፣ በዚህም በተለያዩ ሀገር ያሉ የቢና ገዢዎች ምርጥ የሆነውን በጨረታ እንዲገዙ ይደረጋልም ተብሏል፡፡
ይህ መርሃ ግብር ከኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ክልሎች የሚገኙትን እጅግ አስደናቂ ቡናዎች ለመለየት እና ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑን ተጠቅሷል፡፡

ይህ ቡና ገዢዎች ተጫርተው የሚገዙበት መንገድ የፓናማን፣ የኮሎምቢያን የቡና ገበያ እንዲያድግ ማድረጉን አቶ አሸናፊ ጠቅሰዋል፡፡
ማህበሩ ከኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ያሉ ምርጥ የቡና ዝርያዎችን የመለየት እና የማስተዋወቅ ሀገራዊ ስራን ይመራል፣ ለዕውቀት ሽግግር፣ ለምርምር፣ ለሙያ መጎልበት፣ ለገበያ እድል መስፋፋት እንደ ማዕከል ሆኖ ያገለግላል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ማህበር መመስረት አርሶ አደሮችን፣ ላኪዎችን፣ የህብረት ስራ ማህበራትን፣ ተመራማሪዎችን፣ ቡና ቆይዎችን እና የመንግስት አጋሮችን ያገናኘ ሲሆን ይህም የኢትዮጵያ ቡናን ወደ አዲስ የልህቀት ምዕራፍ የሚወስድ እና አለም አቀፍ ትብብርን ነው ሲባልም ሰምተናል፡፡

የኢትዮጵያ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ አርጋው "የባለ ልዩ ጣዕም ቡናን ማሳየት፣ የምርቱን የመከታተያ እና የጥራት ደረጃዎችን ማጠናከር እንዲሁም አምራቾች በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ ማድረግ ላይ አንሰራለን ብለዋል፡፡
ገበሬውን በሥልጠና፣ በትምህርት፣ በምርምር እና በጥራት ላይ ያተኮሩ የልማት ፕሮጀከቶችን በማበርታት፣ የቡና ማህበረሰብ አቅም እንዲበረታ ማህበሩ ልሰራ አቅጀለሁ ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ማኅበር አባል አቶ ፋይሰል አብዶሽ "ተልዕኳችን የኢትዮጵያን ልዩ ቡና እንደገና መበየን፣ መጠበቅ፣ ማስተዋወቅ እና መሸለም ነው" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዘንድሮ 600,000 ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 3 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት አስባለች፡፡
በበጀት ዓመቱ ሶስት ወራትም 114,000 ቶን ቡና በመላክ 762.5 ሚሊየን ዶላር ተገኝቷል መባሉ ይታወሳል፡፡
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s








