ኢትዮ ቴሌኮም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 215.8 ቢሊዮን ብር ገቢ አገኘሁ አለ።
- Jul 23
- 1 min read
ሐምሌ 16 2018
ኢትዮ ቴሌኮም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 215.8 ቢሊዮን ብር ገቢ አገኘሁ አለ።

የደንበኞች ቁጥርም ባለፈው ዓመት ከነበረበት በ8.3 በመቶ አድጎ 90.1 ሚሊዮን ደርሶልኛል ብሏል።
ተቋሙ ይህንን ያለው የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀሙን በተመለከተ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
በበጀት አመቱ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የተናገሩት የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በዓመቱ 215.8 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን አንስተዋል።
ይህም የእቅዱን 99.7 በመቶ ነው ብለዋል፡፡ ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲመሳከር ደግሞ የ33.2 በመቶ እድገት ከፍ ያለ ነው።
ለተመዘገበው ከፍ ያለ ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ ካበረከቱ የአገልግሎት ዓይነቶች መካከል ቀዳሚው ኢንተርኔት አገልግሎት 31በመቶ ድርሻ ሲኖረው በሁለተኛነት የሞባይል ድምፅ አገልግሎት 23 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡
በበጀት ዓመቱ 603 አዳዲስ የተቋሙ ኔትወርክ ማሰራጫ የሞባይል ጣቢያዎች ወደ ሥራ ገብተው አጠቃላይ ቁጥራቸው 10,613 ደርሷል ይህም 1.5 ሚሊዮን አዳዲስ ተጠቃሚዎችን አገልግሎቱን እንዲያገኙ መደረጉን ሰምተናል።
በተጠናቀቀው በጀት አመት 264 ተጨማሪ ከተሞች የ4ጂ አገልግሎት ተጠቃሚ ሲሆኑ 4ጂ ሽፋን 82.2 በመቶ ደርሷል።
7 አዳዲስ ከተሞች ደግሞ የ5ጂ አገልግሎት በማግኘታቸው አጠቃላይ 33 ከተሞች ተጠቃሚ እንደሆኑ ተነግሯል።
በተመሳሳይ በቴሌብር የ4.1 ትሪሊዮን ብር የገንዘብ ዝውውር ተደርጓል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ አጠቃላይ የቴሌብር ተጠቃሚዎች ቁጥር ደግሞ ከ60 ሚሊዮን ተሻግሯል ብለዋል።
የቴሌብር አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞችም ቁጥር ከባለፈው ዓመት በ12.71 ሚሊዮን መጨመሩን ያነሱ ሲሆን በቴሌ ብር በቀን እስከ 11 ቢሊዮን ብር የሚደርስ የገንዘብ ዝውውር ይደረጋል ሲሉ በመግለጫቸው አክለዋል።
በሌላ በኩል ተቋሙ ድርሻውን ለዜጎች ለመሸጥ ባወጣው አክሲዮን ገበያ የአንድ አክስዮን ዋጋ ከ300 ብር ወደ 852 ብር ከፍ ማለቱን ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ከቀረቡ 47ሺ የሚጠጉ የአክሲዮን ግዢ ጥያቄዎች ውስጥ 96 በመቶ የሚሆኑት አክሲዮኖች የባለቤትነት ማረጋገጫ እንደተሰጣቸው አስረድተዋል።
ማርታ በቀለ
_edited.jpg)


Comments