top of page

አቶ መስፍን ኤልዶ «85 ሺህ ብር ከባንክ ሒሳቤ የተወሰደብኝ ስልኬ በጠፋ በ4ኛው ቀን ነው» ይላሉ።

  • 6 hours ago
  • 2 min read

ነሐሴ 12 2018


አቶ መስፍን ኤልዶ «85 ሺህ ብር ከባንክ ሒሳቤ የተወሰደብኝ ስልኬ በጠፋ በ4ኛው ቀን ነው» ይላሉ።


«ስልኬ ቅዳሜ ዕለት ተሰረቀ። ወዲያው ባንክ ሄጄ የባንክ ሒሳቤ እንዳይንቀሳቀስ አሳገድኩ፤ የባንክ ምስጢር ቁጥሬን ከእኔ ውጪ ማንም አያውቅም፤ የስልክ ቀፎዬ ላይም አልጻፍኩም። የባንክ ሒሳቤንም ያሳገድኩት እንደው ለምናልባቱ ብዬ እንጂ የባንክ ሒሳቤ ይመዘበርብኛል ብዬ አልነበረም» በማለት ያስረዳሉ።




ቅዳሜ ዕለት ያሳገዱትን የባንክ ሒሳብ ሰኞ ዕለት ካስከፈቱ በኋላ በነገታው ማክሰኞ 85 ሺህ ብር ተወስዶባቸዋል።


ሌላኛው ተጎጂ አቶ በለጠ ሙላት ደግሞ የስልክ ቀፎ ሳይሆን የሲም ካርድ ከተሰረቀባቸው በኋላ 120 ሺህ ብር ከሒሳብ አካውንታቸው እንደተዘረፈ ነግረውናል።


«ከእኔ የወጣው ብር ወደ አራት ሰዎች የሒሳብ አካውንት እንደተዘዋወረ ባንኮች አረጋግጠውልኛል» ብለውናል። ነገር ግን ገንዘቡ የተዘዋወረላቸው ሰዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር ሊውሉ አልቻሉም።


በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲህ ዓይነት ወንጀሎችን የሚመረምሩ ፖሊሶችን አነጋግረናል። መርማሪ ፖሊሶቹ ስማቸው እንዲጠቀስ፣ ድምፃቸውም እንዲቀዳ አልፈቀዱልንም።


ይሁን እንጂ አንደኛው መርማሪ ፖሊስ አራት እንዲህ ዓይነት የባንክ ሒሳብ ምንተፋ ወንጀሎች እንደገጠሟቸው ነግረውናል።


«እንዳለመታደል ሆኖ አራቱንም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ማዋል አልቻልንም» ይላሉ።


«አንደኛው ተጠርጣሪ ያልተያዘበት ምክንያት ገንዘቡ ከተጎጂ የባንክ ሒሳብ ተነስቶ መጨረሻ ላይ የተላለፈለት ሰው የባንክ ሒሳብ ቁጥር የተከፈተው በሕይወት በሌለ ሰው ሲም ካርድ በመሆኑ ነው» ይላሉ።


«ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ መጨረሻ ላይ በቁጥጥር ሥር ያዋልናት ሴት ሲም ካርዷ ጠፍቶ የባንክ ሒሳቡ በእሷ ሲም ካርድ የተከፈተ እንጂ ወንጀሉ ውስጥ እንደሌለችበት አረጋግጠን ለቀቅናት» ብለውናል።


«ሌላኛው መጨረሻ ላይ ገንዘብ የተላለፈለት የባንክ ሒሳብ የተከፈተው ሀገር ውስጥ በሌለ ሰው ሲም ካርድ በመሆኑ በቁጥጥር ሥር ማዋል አልቻልንም» ይላሉ።


«አንዳንድ የባንክ ሠራተኞች በዚህ የወንጀል ድርጊት ውስጥ እንዳሉበት በቂ መረጃ ቢኖረንም፣ ግን ማስረጃ የለንም» ይላሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ መርማሪ ፖሊስ። የባንክ ሠራተኞቹ ማስረጃ ያጠፉብናል ይላሉ።


ባንኮች በዚህ ረገድ የአሠራር ሥርዓታቸውን እንዲፈትሹ እና ለደንበኞቻቸው ሀብት ደህንነት ዋስትና እንዲሰጡም ይመክራሉ።


የፋይናንስ ደህንነት ባለሙያው አቶ አይቸው አደፍርስ «መንታፊዎች የአንድን ሰው የባንክ ሒሳብ ምስጢር ቁጥር የሚሰብር መተግበሪያ አላቸው፤ ይህንም ደርሰንበታል» ይላሉ።


ይህ መተግበሪያ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ታግዞ ባለ 4 ዲጂት ምስጢር ቁጥሮችን በሰከንድ ውስጥ እስከ 1 ቢሊዮን ድረስ ከገመተ በኋላ ከግምቶቹ በአንዱ ምስጢር ቁጥር ሰብሮ ሊገባ ይችላል በማለት ያስረዳሉ።


ይሁን እንጂ የባንኮች አሠራር ለእንዲህ ዓይነቱ ግምት የሚመች አይደለም። ምክንያቱም የአንድን የባንክ ሒሳብ ቁጥር ምስጢር ቁጥር ለመገመት የባንክ አሠራሩ ከሦስት ጊዜ በላይ የዘለለ ዕድል አይሰጥም።


ባለሙያው አቶ አይቸው ግን «እንዲህ ዓይነቱ ምዝበራ የሚካሄደው በቴክኖሎጂው ላይ የረቀቀ ዕውቀት ባላቸው ሰዎች ስለሆነ ለዚህ መላ አላቸው» ይላሉ።


ባለአራት ዲጂት ምስጢር ቁጥር በቀላሉ ስለሚገመት ባንኮች የምስጢር ቁጥራቸውን ዲጂት እንዲያበዙ አማክረን ነበር ይላሉ።


ነገር ግን ባንኮች «ዲጂት ሲበዛ ደንበኞች ይቸገራሉ፣ ከባንክም ይርቃሉ» በሚል ሰበብ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ያስረዳሉ።


ባንኮች ትልቅ ትኩረት ሰጥተው ደህንነታቸው ላይ ካልሠሩ መጪው ዘመን ብዙ ፈተና አለው በማለት ባለሙያው ያስጠነቅቃሉ።


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ.....



ንጋት መኮንን

Recent Posts

See All
የነሐሴ 12 የውጪ ሀገር ወሬዎች

#ሩሲያ የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ብሪታንያን በብርቱ አስጠነቀቋት፡፡ ፑቲን ብሪታንያ ለዩክሬይን ግዛት ተሻጋሪ ድሮኖችን ከማቀበል ብትቆጠቢ ይሻልሻል ማለታቸው ሬውተርስ ፅፏል፡፡ ቀደም ሲል ታይምስ ጋዜጣ ዩክሬይን በሩሲያ ላይ ግዛት ተሻጋሪ ጥቃት የምታደርሰው በብሪታንያ ስሪት ድሮኖች እንደሆነ መዘገቡ ተጠቅሷ

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page