top of page

አስፈጻሚው የመንግስት አካል በግለሰቦች ላይ በደል ሲፈፅም የሚቀጣበት የአስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጅ ስራ ላይ ቢሆንም ብዙዎች ነገሬ ብለው እንደማይጠቀሙበት በጉዳዩ ላይ የሚሰሩ የህግ ባለሙያዎች ነግረውናል፡፡

  • 1 hour ago
  • 2 min read

ነሐሴ 13 2018


አስፈጻሚው የመንግስት አካል በግለሰቦች ላይ በደል ሲፈፅም የሚቀጣበት የአስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጅ ስራ ላይ ቢሆንም ብዙዎች ነገሬ ብለው እንደማይጠቀሙበት በጉዳዩ ላይ የሚሰሩ የህግ ባለሙያዎች ነግረውናል፡፡


አዋጁን የማስፈፀም ስልጣን የተሰጠው የፍትህ ሚኒስቴር ይህንን ጉዳይ ለመዳኘት በፌድራል ፍርድ ቤት  የአስተዳደር ጉዳይ ችሎት ቢደራጅም በቂ አለመሆኑን  ነግሮናል፡፡


 የመንግስት ተቋማት የግለሰቦች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም የመከልከል፤ያለአግባብ ከስራ ማባረርና መሰል አስተዳደራዊ በደል ሲፈፅሙ ግለሰቡ የመንግስትን አካል ህግ ፊት አቁሞ መብቱን ማስከበር የሚያስችለው ይህ አዋጅ ስራ ላይ ከዋለ 6 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡


በአዋጁ መሰረት አንድ በደል ደርሶብኛል የሚል ግለሰብ በመጀመሪያ በደል ባደረሰበት ተቋም ውስጥ ላለ ቅሬታ ሰሚ ክፍል ጉዳዩን ያቀርባል፤ቅሬታው አጥጋቢ ምላሽ ካላገኘ የተሰጠውን ምላሽ ይዞ ወደ አስተዳደር ጉዳይ ችሎት ያለራል ያሉን የህግ ባለሙያው አቶ አንዷለም በእውቀቱ በብዛት የሚገጥሟቸውን ጉዳዮች ሲያስረዱ አዋጁ በደሉ በተፈፀመ በ30 ቀናት ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት ቢልም፤ጉዳዩ ወደ ህግ ከቀረበ በኋላ ፍርድ ቤት በደል ፈፃሚውን ተቋም ቅሬታውን ስለመቀበሉ እንዲያረጋግጥ ቢልክም ሆን ብሎ ቅሬታውን ያለመቀበል ችግር አለ፤በዚህ መሃል 30 ቀን ያልፍና ጉዳዩ ውድቅ የሚሆንበት አጋጣሚም እንደሚኖር ይናገራሉ፡፡


ሌላኛዋ የህግ ባለሙያ ትሩፋት በላይነህ በዚህ ጉዳይ ላይ እንደመስራታቸው የአዋጁ ክፍተት ነው ያሉትን ሲያስረዱ አንድ ተበዳይ የበደለውን የመንግስት መስሪያቤት ለመክሰስ የግድ በመስሪያ ቤቱ ደረጃ ጉዳዩ አለመፈታቱን ማረጋገጫ መያዝ ይኖርባቸዋል፤ነገር ግን በተግባር እየገጠመን ያለው ምላሽ ለመስጠት አይደለም የቅሬታ ክፍል ቢኖራቸውን በደሉን መስማት የማይፈልጉ መስሪያ ቤቶች አሉ፤ በዚህ ጊዜ እንዴት ነው ተበዳዩ ፍትህ የሚያገኘው ለሚለው አዋጁ ምላሽ የለውም ይላሉ፡፡


ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው በፍትህ ሚኒስቴር የህጎች ተፈፃሚነት ዳይሬክተሩ አቶ ሲሳይ አስፋው ይህ በህግ አካላት የሚታይ ነው፤የፍትህ ሚኒስቴር ተግባር አይደለም በማለት በተግባር ያለውን ሲያስረዱ እርግጥ ነው መልስ ለመስጠት ዳተኛ የሆኑ የመንግስት ተቋማት አሉ ነግር ግን ተቋሙ ለተከሰሰበት ጉዳይ መልስ ካልሰጠ ጉዳዩ በሌለበት ታይቶ የሚወሰንበት አሰራር እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡


የህግ ባለሙያዎች የሚያነሱት አሁን ስለ አዋጁ በጥቂቱም ቢሆን ግንዛቤ እንዳለና፤መንግስትን መክሰስ እንደሚቻል የገባቸው ተበዳዮች አሁን ካለው በላይ ቢሆኑ የሚስተናገዱበት በቂ ችሎት አለመሆኑን ነው፡፡


በፍትህ ሚኒስቴር የህጎች ተፈፃሚነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ሲሳይ አስፋው በበኩላቸው እውነት ነው በፌደራል ደረጃ ካሉት ሁለትና ሶስት የአስተዳደር ችሎቶች ውጪ በቂ ችሎት የለም ይህንን ማስፋት ያስፈልጋል፤በጠቅላይ ፍርድ ቤት በኩል ቢሰራበት ብለዋል፡፡


የአስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጅ መተግበር ከጀመረ ወዲህ በስራችሁ ያሉ የመንግስት ተቋማት እንዴት እየሰሩበት እንደሆነ ትፈትሻላችሁ ወይ ያልናቸው አቶ ሲሳይ 46 ተቋትን ስራ ክንውን ገምግመናል፤ በመጀመሪዎች ጊዜያት አዋጁን የመረዳት ችግር ነበር፤አሁን ከ46ቱ በከፊል እየፈፀሙ ያሉ አሉ፤5 ተቋት ክፍተት የታየባቸው በመሆኑ በሚቀጥለው አመት በድጋሚ ምልከታ እናደርግባቸዋለን ብለዋል፡፡


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ....




ምንታምር ጸጋው

Recent Posts

See All
ተማሪዎች የሰው ሠራሽ አስተውህሎት (AI) አጠቃቀም ላይ ከመምህራኖቻቸው ቀድመው የሚገኙ ከሆነ በመማር ማስተማር ሂደት ላይ ክፍተት መፍጠሩ አንደማይቀር ተጠቆመ።

ነሐሴ 12 2018 ተማሪዎች የሰው ሠራሽ አስተውህሎት (AI) አጠቃቀም ላይ ከመምህራኖቻቸው ቀድመው የሚገኙ ከሆነ በመማር ማስተማር ሂደት ላይ ክፍተት መፍጠሩ አንደማይቀር ተጠቆመ። ችግሩን ለመቅረፍ መምህራንን በቴክኖሎጂው ማብቃትና AIን በራሱ እንደ አንድ የትምህርት ኮርስ አዋህዶ መስጠት እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ተመ

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page