"አሁን ያለው የፌደራሊዝም ስርዓት የተወሰነ ማሻሻያ ተደርጎበት ይቀጥል" የሚለው ሀሳብ በአብዛኞቹ ተመካካሪዎች መነሳቱን ያነጋገርናቸው የአገራዊ ምክክር ጉባዔተኞች ተናገሩ።
- 17 hours ago
- 2 min read
ሐምሌ 24 2018
"አሁን ያለው የፌደራሊዝም ስርዓት የተወሰነ ማሻሻያ ተደርጎበት ይቀጥል" የሚለው ሀሳብ በአብዛኞቹ ተመካካሪዎች መነሳቱን ያነጋገርናቸው የአገራዊ ምክክር ጉባዔተኞች ተናገሩ።
16ኛ ቀኑን ትናንት ሐምሌ 23 ቀን 2018 ዓ.ም የያዘው የምክክር ጉባዔ፣ በጥቃቅን እና ንዑሳን ቡድኖች የተነሱ ምክረ ሀሳቦች 250 አባላት ላሉት ስልታዊ ቡድን በቀረቡበት ወቅት ሳይካተቱ የቀሩ ተጨማሪ ምክረ ሀሳቦችን ሲቀበል ውሏል።
ተጨማሪ ምክረ ሀሳቦችን ሲቀበሉ ካረፈዱ ስልታዊ ቡድኖች ውስጥ አንዱ የመንግስት አደረጃጀት እና የፖለቲካ ስርዓት አጀንዳ ላይ የሚወያየው ቡድን ሁለት ነው።
በዚህ ቡድን ስር "የመንግስት ስርዓት ምን ይሁን?" ለሚለው ጥያቄ ሶስት አማራጮች መቅረባቸውን ተሳታፊዎች ነግረውናል።
እነሱም አህዳዊ፣ ፌደራላዊ እና ኮንፌደራል የሚሉ መሆናቸውን፣ የሚሰጡ ምክረ ሀሳቦችን የማጠናከር ስራ የሚሰሩት እና በቡድኑ ውስጥ የስብሳቢነት ድርሻ ወስደው እየሰሩ የሚገኙት አቶ ሰሎሞን ገብሬ ያስረዳሉ።
አቶ ሰሎሞን ፤ "አህዳዊ ስርዓት" የሚለው አማራጭ ምክረ ሀሳብ አገሪቱ ከዚህ ቀደም ያለፈችበት ስለሆነ ውጤቱም ስለታየ "ምክረ ሀሳቡ በሚበዙት ተሳታፊዎች አልተደገፈም"፤ በተመሳሳይ "የኮንፌደራል" የሚለው አማራጭ ደግሞ ውስብስብ በመሆኑ፣ እንዲሁም አገሪቱ አሁን ካለችበት የብሔሮች አወቃቀር አንጻር ተግባራዊ ለማድረግ ስለሚከብድ "በስራ ላይ ያለው የፌደራል ስርዓት ያሉበት ችግሮች ተስተካክለው ይቀጥል" የሚለው ሀሳብ በበርካታ ተሳታፊዎች መነሳቱን አስረድተዋል።
ካሉት የፌደራሊዝም ዓይነቶች ውስጥ ደግሞ ቋንቋን መሰረት ያደረገ ይሁን ወይስ የመልካዓ ምድር አቀማመጥን (ጂኦግራፊን) መሰረት ያደረገ ይሁን በሚል ደካማ እና ጠንካራ ጎናቸው ተዘርዝሮ መቅረቡን ተሳታፊው አስታውሰዋል።
"አሁን በስራ ላይ ያለው የፌደራሊዝም ስርዓት ደካማ ጎኖች ተብለው የተዘረዘሩት የትኞቹ ናቸው?" ብለን የጠየቅናቸው አቶ ሰሎሞን፤ የንብረት መብት እንዳይከበር ማድረጉ፣ በጎሳ መከፋፈሉ፣ ሰዎች ተንቀሳቅሰው እንዳይሰሩ ማድረጉ፣ እንዲሁም "ይህ ያንተ አይደለም" በሚል ሰዎች ከቄያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉ የሚሉት ከዘረዘሯቸው በርካታ ችግሮች መካከል ጥቂቶቹ መሆናቸውን ነግረውናል ።
"አሁን በስራ ላይ ያለው የፌደራሊዝም ስርዓት ያሉበት ችግሮች ወይም ደካማ ጎኖች ተሻሽለው ይቀጥሉ" የሚል ምክረ ሀሳብ በአብዛኛው መነሳቱን ተመካካሪው ተናግረዋል።
ይህ ማለት ግን ምክረ ሀሳቡ ሙሉ በሙሉ በጉባዔተኛው ጸድቋል ማለት አይደለም።
መጋቢ አዲሱ አሰፋ የተባሉ ሌላው ተመካካሪም እየተሳተፉበት በሚገኙት ርዕስ ስር፣ አብዛኛው ተሳታፊ "አሁን ያለው የፌደራሊዝም ስርዓት ተሻሽሎ ይቀጥል" የሚል ሀሳብ ማንሳቱን ይናገራሉ።
"የመንግስት አስተዳደር ስርዓትስ የትኛው ይሁን?" ለሚለውም ሶስት አማራጮች ቀርበዋል። እነሱም ፓርላሜንታዊ፣ ፕሬዚዳንታዊ እና የሁለቱ ቅይጥ (ሴሚ-ፕሬዚዳንሻል) ናቸው።
ከጋምቤላ ክልል ተወክለው መሳተፋቸውን የነገሩን አቶ ሰይማን ቱት፣ እሳቸው ከቀረቡት ሶስት ዝርዝሮች ውስጥ "ፕሬዚዳንታዊ ይሁን" የሚል ምክረ ሀሳብ ማቅረባቸውን ጠቅሰው፤ አብዛኛው ተሳታፊ ግን "አሁን ያለው ፓርላሜንታዊ ስርዓት ችግሮቹ ተስተካክለው ይቀጥሉ" የሚል ሀሳብ ማንሳቱን ነግረውናል።
አቶ ሰሎሞን በበኩላቸው፤ "ጠቅላይ ሚኒስትር" የሚለው ቀርቶ አገሪቱ በፕሬዚዳንት ትተዳደር፣ አንድ ርዕሰ ብሔርም ይኑራት፣ ወይም እኩል ስልጣን ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር እና ፕሬዚዳንት ይኑሩ የሚሉ እና ሌሎች አማራጮች መቅረባቸውን ነግረውናል።
ተመካካሪው ፕሬዚዳንቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሀላፊነት ወስዶ ይስራ (ልክ እንደ ደቡብ አፍሪካ ስርዓት)" የሚለው አንዱ አማራጭ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
ሌላው አማራጭ ደግሞ "ሁለቱም ይኑሩ፤ ማለትም ፕሬዚዳንትም ጠቅላይ ሚኒስትርም ይሁኑ፤ ነገር ግን ተጠያቂነቱንም ሆነ የስራ ድርሻውን ሁለቱም ይከፋፈሉ" የሚለው ነው ሲሉ አስረድተዋል።
እነዚህ ምክረ ሀሳቦች የሚጸድቁት 500 አባላት ላሉት ቡድን ቀርበው በአብዛኛው ሰው ከተደገፉ ነው።
እስካሁን ውይይት እየተደረገባቸው ላሉት 8ቱም አጀንዳዎች የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች አንዳቸውም አልፀደቁም።
ያሬድ እንዳሻው
_edited.jpg)



Comments