top of page

ነሐሴ 8፣2016 - ነሐሴ 8፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Aug 14, 2024
  • 2 min read

 

ኤም ፖክስ(Mpox) የተሰኘው የፈንጣጣ በሽታ በአፍሪካ አህጉር የህዝብ የጤና ስጋት መሆኑ ታወጀ፡፡

 

ወረርሽኙ አህጉራዊ የጤና ስጋት ነው ሲል ያወጀው የአፍሪካ የበሽታዎች ቁጥጥር እና መከላከል አካል (Africa CDC) እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡

 

ባለፉት 8 ወራት በአህጉሪቱ ከ13 ሺህ 700 በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል፡፡

 

450 ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ ሕይወታቸው ማለፉ ታውቋል፡፡

 

ኮንጎ ኪንሻሣ የወረርሽኙ ተፅዕኖ ያየለባት አገር ነች፡፡

 

ቡሩንዲ ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፖብሊክ ፣ ኬኒያ እና ሩዋንዳም በበሽታው  የተያዙ ሰዎች የተገኙባቸው ናቸው፡፡

 

በሽታው እንደ ሌሊት ወፍ ካሉ እንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ ነው፡፡

 

በአካላዊ ንክኪ እና በትንፋሽም ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ተጠቅሷል፡፡

 

ወረርሽኙ አህጉራዊ የጤና ስጋት ነው ተብሎ መታወጁ መንግስታት ለመከላከሉ ትኩረት እንዲሰጡ እና ሐብት እንዲያሰባስቡ ይረዳል ተብሏል፡፡


የሱዳን ወታደራዊ መንግስት ተወካዮች በጄኔቫ ስዊዘርላንድ በሚካሄደው የሰላም ንግግር ሳይገኙ ቀሩ፡፡

 

በምህፃሩ RSF የተሰኘው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ለሰላም ንግግሩ ተወካዮቹን ወደ ጄኔቫ እንደላከ ሱዳን ትሪቢዩን ፅፏል፡፡

 

የሱዳን መንግስት ጦር እና  RSF ጦርነት ማካሄድ ከጀመሩ አመት ከ4 ወራት ሊሆናቸው ነው፡፡

 

የተባበሩት መንግስታት ፣ የአፍሪካ ህብረት ለሰላም ንግግሩ ተወካዮቻቸው ከላኩት መካከል ናቸው ተብሏል፡፡

 

ግብፅም ልዑካን ወደዚያ መስደዷ ታውቋል፡፡

 

የሱዳን ተፋላሚዎችን የሰላም ንግግር ከዛሬ አንስቶ ለመጀመር ታቅዶ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

 

የሱዳን ወታደራዊ መንግስት አማፂ ሲል የጠራው RSF ከያዛቸው ከተሞች ተጠራርጎ ካልወጣ በንግግሩ አልሳተፍም ማለቱ ታውቋል፡፡

 

በጄኔቫው ንግግር የሱዳን መንግስት ጦር ተወካዮች አለመገኘት የውጤታማነቱን ነገር ሲበዛ አጠራጣሪ ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡

 

 

በሊቢያ ፖለቲካዊ ቀውሱ እየተባባሰ ነው ተባለ፡፡

 

መሰረቱን በአገሪቱ ምስራቅ ያደረገው ፓርላማ መቀመጫው በትሪፖሊ የሆነውን የጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሐሚድ ድቤይባን መንግስት የሀላፊነት ጊዜው አብቅቷል የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡

 

ከዚህም በተጨማሪ ፓርላማው አዲስ የብሔራዊ አንድነት መንግስት እስኪሰየም የምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ካቢኔ መንግስታዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ ይቆያል ማለቱ ተሰምቷል፡፡

 

ሊቢያ የቀድሞው መሪ የኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ አስተዳደር በትጥቅ አመፅ ከተወገደ ወዲህ ሥርዓተ አልበኝነት እንደነገሰባት ነው፡፡

 

መንግስታዊ አስተዳደሯም በምዕራብ እና በምስራቅ እንደተከፋፈለ ነው፡፡

 

አሁን ደግሞ የሊቢያ የፖለቲካ ተቀናቃኞች ወደ ጦርነት ለመመለስ ዳር ዳር እያሉ መሆኑ ይነገራል፡፡

 

 

የፍልስጤም ራስ ገዝ አስተዳደር ፕሬዘዳንት ማሃሙድ አባስ የፍልጤስም ነፃ አገራዊ መንግስት ያለመመስረቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቱ ዋነኛው ድክመት ነው አሉ፡፡

 

ማሐሙድ አባስ በዚህ ጉዳይ ያማረሩት በሞስኮ ከሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በተነጋገሩበት ወቅት እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡

 

አባስ የፍልስጤምን ነፃ አገርነት የማወጁ ተግባር ለተባበሩት መንግስታት ያን ያህል የከበደ አልነበረም ብለዋል፡፡

 

ሆኖም ድርጅቱ በአሜሪካ ተፅዕኖ ስር መውደቁ አቅመ ቢስ እንዳደረገው የፍልስጤማውያኑ ፕሬዘዳንት ተናግረዋል፡፡

 

አባስ ሩሲያ ለፍልስጤማውያን ለምታደርገው እና ስታደርገው ለቆየችው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል ተብሏል፡፡

 

ለእስራኤል እና ለፍልስጤማውያን ነባር ችግር ዘላቂው መፍትሄ የሁለት መንግስታት መሳ ለመሳ መኖር ነው ቢባልም የሀሳቡ ስራ ላይ መዋያ በጭራሽ እንደማይታይ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡

 

የኔነህ ከበደ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page