ነሐሴ 15 2017 - ታሪክን የኋሊት -ሚኻኤል ጎርቫቾቭ ላይ የተሞከረው መፈንቅለ መንግስት
- sheger1021fm
- 6 hours ago
- 1 min read
የሶቪየት ህብረት ፕሬዝዳንት በነበሩት ፣ ሚኻኤል ጎርቫቾቭ ላይ የተሞከረው መፈንቅለ መንግስት የከሸፈው በ1983 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡
የሶቪየት ህብረት ኮሚዩኒስት ፓርቲ ዋና ፀሐፊና ፕሬዘዳንት ላይ መፈንቅለ መንግስት የሞከሩት ምክትል ፕሬዘዳንታቸውና ሌሎች የፖሊት ቢሮ አባላት ናቸው፡፡
ጎርቫቾቭ ፣ ለ60 አመታት የዘለቀውን የሶቪየት ህብረት ኮሚዩኒስታዊ ሥርዓት ለማሻሻል የነደፉት ፖሊሲ አክራሪ በሚባሉት ሹማምንት አልተወደደላቸውም፡፡
ባልተለመደ አሰራር ፣ ዜጎች የመሰላቸውን በነፃነት እንዲናገሩ ፣ የስራ ሀላፊዎች በጉድለታቸው እንዲጠየቁ ለማድረግ የጀመሩት የግልፅነትና የነፃነት እንቅስቃሴ፣ በፓርቲው ሀላፊዎች የተነቀፈ ሆነ፡፡
ሶቪየት ህብረት የተመሰረተችበትን አቋም ያናጋል፣ በምዕራባውያን ፍላጎት ስር ይጥላታል የሚል ፍራቻ ነበራቸው፡፡
ሕዝቡ ግን፣ በጋለ ድጋፍ ጎርቫቾቭን፣ ከዚያ በላይ እንደገፉን አበረታታቸው፡፡

በቀዝቃዛው ጦርነት ተፋጠው የነበሩት ምዕራባዊያን መንግስታትና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው ጎርቫቾቭን “ጎርቢ” በሚል ቅፅል እያወደሱ ድጋፍ ሰጧቸው፡፡
ምክትል ፕሬዘዳንቱ ያሉበት የፖሊት ቢሮ አባላት ፣ ጎርቫቾቭ ክራሚያ ለእረፍት በሄዱበት ከስልጣን እንደተወገዱ ነገሩዋቸው፡፡
ወታደሮችንና ታንኮችን በሞስኮ አደባባይ አሰለፉ፡፡
እቅዳቸው የተዝረከረከና ያልተቀናጀ ነበር፡፡
ሕዝቡም ተቃወማቸው፡፡
የሩሲያው ፕሬዚዳንት፣ ቦሪስ የልሲን ህዝቡን አስተባብረው ፣ የተቃውሞ ሰልፉ እንዲጋጋል አደረጉት፡፡
ወታደሮችም የህዝቡን ተቃውሞ በሀይል ለማስቆም አልፈለጉም፡፡
ስለዚህ ፣ በሶስተኛው ቀን የልሲን የሚመሩት ሕዝባዊ ተቃውሞ የበላይነት አገኘ፡፡
የአድማውን መሪዎች ተያዙ፡፡
የሃገር ሚኒስትሩ ራሳቸውን ገደሉ፡፡
ጎርቫቾቭ እዚው እንደቆዩ ከተገደዱበት የእረፍት ቦታቸው፣ ወደስልጣናቸው ተመለሱ፡፡
ግን አመፁ ቢከሽፍም፣ የጎርቫቾቭን ስልጣንና ሶቪየት ህብረት ግዛቶች አንድነት ለማዳን አልቻለም፡፡
ሩሲያው ፕሬዘዳንት ቦሪስ የልሲን፣ ሀይልና አገኙና፣ ጎርቫቾቭን የማያዳምጡ ሆኑ፡፡
ጎርቫቾቭን ሲያሞግሷቸው የነበሩት፣ ምዕራባዊያንም፣ ድጋፋቸው ወደ የልሲን አዙሩ፡፡
ሶቪየት ህብረት እንድትፈራርስ ስለሚፈልጉ፣ ጎርቫቾቭን የውሃ ላይ ኩበት አደርጓቸው፡፡
ከአምስት ወራት በኋላም ስልጣናቸው ለቀቁ፡፡
ሶቪየት ህብረት የምትባል አገር ተባታትና፣ የህብረቱ ግዛቶች ለየራሳቸው ሃገር ሆኑ፡፡
የመፈንቅለ መንግስቱ መክሸፍ ፣ የሶቪየት ህብረት መጨረሻ ሆነ፡፡
የሶስት ቀናቱ የሶቪየት ህብረት መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ከከሸፈ ፣ 24 ዓመት ሆነ፡፡
እሸቴ አሰፋ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
Comments