ነሀሴ 8 2017 - የሽግግር ፍትህ ሲያሰናዳ የቆየው የህግ ባለሙያዎች ቡድን ስራ ማቆሙ ተሰማ፡፡
- sheger1021fm
- Aug 14
- 2 min read
የሽግግር ፍትህን ስራ ላይ ለማዋል የተለያዩ የህግ ረቂቆችን ሲያሰናዳ የቆየው የህግ ባለሙያዎች ቡድን ስራ ማቆሙ ተሰማ፡፡
#የሽግግር_ፍትህ ላይ እየተከወነ ያለው ስራ “ለጊዜው ይቆይ” የሚል እና ይፋዊ ያልሆነ በቃል ብቻ መመሪያ በመስጠቱ የባለሞያ ቡድኑ ስራውን ካቆመ 4 ወር እንዳለፈው ሰምተናል፡፡
የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ፍትህ ሚኒስቴርም በግልፅ መረጃ ሊሰጠን አልፈቀደም፡፡
ከዓመት በፊት የፀደቀውን የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ለማስፈፀም ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር ሲሰራ የቆየው የህግ ባለሞያዎች ቡድን 5 የህግ ረቂቆችን አሰናድቶ ማጠናቀቁን ሰምተናል፡፡
ስሜ ይቅር ያሉ እና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጫችን እንዳሉት የህግ ረቂቆቹ አልቀው ፍትህ ሚኒስቴር ባሰናዳው አለም አቀፍ ኮንፍረንስም ግብዓት ተሰብስቦባቸዋል፡፡

በሃገር ውስጥ ግብዓት ለማሰባሰብ ቦታዎች ተለይቶ መንግስትም 100 ሚሊዮን ብር ከመደበ በኋላ ግን ባልታወቀ ምክንያት በቃል ብቻ ለህግ አርቃቂው ቡድን “ለጊዜው ስራው ይቁም ተብሏል” የሚል መረጃ ተነግሮት ስራውም በዚያው መቆሙን ከምንጫችን ሰምተናል፡፡
ፍትህ ሚኒስቴም ሆነ የህግ አርቃቂው ቡድን ድንገተኛ የተባለውን ውሳኔ የሰሙት ለረቂቅ ህጎቹ ግብአት ለማሰባሰብ እየሰሩ ባለበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡
በመሆኑም አሁን ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በጋራ የሽግግር ፍትህ ስራውን ለመከወን የሚረዱ ህጎችን ሲያረቅ የቆየው የህግ ባለሞያዎች ቡድን ስራውን ሙሉ በሙሉ አቁመዋል ተብሏል፡፡
ረቂቃቸው ተሰናድቶ ለግብዓት ማሰባሰብ ዝግጁ ሆነው ነበር ከተባሉ የህግ ማዕቀፎች መካከል “የልዩ አቃቤ ሕግ ፅ/ቤት መቋቋሚያ አዋጅ” ፣ በፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤትና በጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር የሚቋቋመው “ልዩ ችሎት የማቋቋሚያ አዋጅ” እንዲሁም “የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን የማቋቋሚያ አዋጅ” ይገኙበታል፡፡
በሽግግር ፍትህ ሂደቱ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል ተብለው የተለዩትን በወንጀል ለመጠየቅም የሚያስችል አዲስ የህግ ረቂቅም ተሰናድቶ ነበር ተብሏል፡፡
የሽግግር ፍትህ ፖሊሲውን አሰናድቶ ከማፅደቅ ጀምሮ ሂደቱ ከፍተኛ የሃገር ሀብት የፈሰሰበት መሆኑም ይታወቃል፡፡
መንግስት ከደለደለው በጀት ባሻገር የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛው የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፉና ሃገር በቀል ተቋማት ድጋፍ ማድረጋቸውንም ሰምተናል፡፡
የእወቁት ደብዳቤም በሌለበት በቃል ብቻ በተሰጠ ትዕዛዝ ለጊዜው ይቁም ተብሏል የተባለው የሽግግር ፍትህ ሂደት መቼ ተመልሶ እንደሚጀምር የታወቀ ነገር የለም፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments