ነሀሴ 7 2017 - በኢትዮጵያ 400 ሜጋ ዋት ሀይልን ከፀሀይ ሀይል ለማመንጨት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።
- sheger1021fm
- Aug 13
- 2 min read
ኢትዮጵያ ከፀሐይ የኤሌክትሪክ ኃይልን የማመንጨት ከፍተኛ አቅም ቢኖራትም፣ እስካሁን ማመንጨት የተቻለው ግን ከ10 ሜጋ ዋት በታች ሀይል መሆኑ ተነግሯል።
በተለይ የግብርናውን ዘርፍ ለማገዝ በነዳጅ ኃይል የሚሰሩ የውሃ መሳቢያ (ፓምፖች)፣ በፀሐይ ኃይል ወደሚሰሩ መቀየር የግድ የሚልበት ጊዜ መሆኑ ተነግሯል።
ኢትዮጵያ ከፀሐይ ኃይል 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይልን ለማመንጨት የሚያስችላትን ስምምነት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢንተርናሽናል ሶላር አሊያንስ ጋር ተፈራርሟል።
በስምምነቱ መሰረት ከ3 እስከ 6 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ፕሮጀክቱ የትኞቹ ቦታዎች ላይ እንደሚሰራ በመለየት የግንባታ ስራ ይጀምራል ተብሏል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ እንዳሉት፤ ከፀሐይ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይልን የማመንጨት አቅም ያላት ኢትዮጵያ እስካሁን ማመንጨት የቻለችው 7.9 ሜጋ ዋት ብቻ ነው።
ይህም የሆነው ዘርፉ ባለፉት ዓመታት የግል ባለሀብት እንዲገባበት የህግ ድጋፍ ያልነበረውና የተከለከለ ስለነበር ነው ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግሉ ዘርፍም እንዲሳተፍ መፈቀዱ ሀይል የማመንጨት ስራ የመንግስት ብቻ መሆኑ እንዲያበቃ አድርጓል ብለዋል።
በተለይ የግብርናው ዘርፍ በዝናብ ላይ ጥገኛ ሆኖ መቀጠሉ የትም አያደርሰንም ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው የግድ በቴክኖሎጂ መታገዝ ይኖርበታል ብለዋል።
የውሃ መሳቢያ መሳሪያ (ፓምፕ) እና ሌላውም የሚሰራው በናፍጣ መሆኑን በማንሳት በነዳጅ ውድነትና በቀላሉ አለመገኘት ምክንያት በዛ መንገድ መቀጠል አይቻልም ብለዋል።
ከዚህ በኋላ ለግብርናው የሀይል አማራጭ በፀሀይ ሀይል የሚመነጭ ኤሌክትሪክ እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል።
አሁን ከኢንተርናሽናል ሶላር አሊያንስ ጋር የተፈረመው ስምምነትም የሚሰራው ግብርና ባለበት እና በገጠሩ አካባቢ እንደሚሆን ተነግሯል።
ስምምነቱን የተፈራረመው ኢንተርናሽናል ግሎባል አሊያንስ ከ10 ዓመት በፊት የተመሰረተ ህብረት ሲሆን መንግስታት በፊርማቸው አባል የሚሆኑበት ነው።
እስካሁንም ኢትዮጵያን ጨምሮ 124 ሀገራት ማህበርተኛ መሆናቸው ተነግሯል።
በተለይም ታዳጊ ሀገራት አካባቢን ከሚጎዳ የሀይል አማራጭ ወደ ታዳሽ የሀይል ምንጭ ለመሸጋገር የሚያደርጉትን ጥረት መደገፍ ቀዳሚ ስራው ነው ተብሏል።
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አሺሽ ካና ሲናገሩ እንደሰማነው በናፍጣ የሚሰራ የውሃ መሳቢያ የሚጠቀም ገበሬ፤ በፀሀይ ሀይል የታገዘ አማራጭን ከሚጠቀመው ወጪው በ4 እጥፍ ይጨምራል።
በዛሬው ዝግጅት ላይ በመኖሪያ ቤት እና ህንፃ ጣሪያ ላይ በሚተከል የፀሀይ ሀይል መሰብሰቢያ ሀይል ለማመንጨት የሚያስችል ስምምነትም ከተቋሙ ጋር ተፈርሟል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ጠንባሮ ልዩ ወረዳ ዋሮ በተባለ መንደር 700 ኪሎ ዋት በሰዓት ሀይል ከፀሀይ የሚያመነጭ ፕሮጀክትን ለመስራትም ከስምምነት መድረሳቸው ይፋ ተደርጓል።
ቴዎድሮስ ወርቁ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments