ነሀሴ 28 2017 - ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት
- sheger1021fm
- 27 minutes ago
- 1 min read
ክልሎች የገጠር ቀበሌ ማዕከላትን በማቋቋም ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትን እንዲቀንሱ ስራ መጀመሩ ይታወሳል።
ስራው በክልሎች የተለያየ አፈጻጸም እንዳለው የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ተናግሯል።
በኢትዮጵያ በከተሞች የሚታየው የህዝብ ዕድገት ምጣኔ ፈጣን ከሚባሉት መካከል እንደሆነ ይነገራል።
ዕድገቱ አሁን ላይ 5.4 በመቶ ስለመሆኑ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
እንደ ጎርጎርሳውያኑ አቆጣጠር ከ2028 እስከ 2034 በኢትዮጵያ ከተሞች የሚኖረው ህዝብ አሁን ካለው በሶስት እጥፍ ይጨምራል ተብሎም ተተንብይዋል።

በሌላ አነጋገር ከአስር ዓመት በኋላ ሠላሣ በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በከተሞች ይኖራል እንደማለት ነው።
ለከተሞች የህዝብ ቁጥር መጨመር ከገጠር ወደ ከተሞች የሚደረግ ፍልሰት አንዱ ምክንያት ሆኖ ይነሳል።
ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ፤ አነስተኛ የእርሻ መሬት እና የመሣሠሉ ምክንያቶች ሰዎች ከገጠር ወደ ከተማ እንዲፈልሱ ከሚያደርጉት መካከል ናቸው።
ይህ በየጊዜው እየጨመረ ያለ ፈልሰት በከተሞች ላይ ከፍተኛ ጫና እያስከተለ ይገኛል የሚለው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ችግሩን ለመቀነስ በሁለት መንገድ እየተሰራ ነው ሲል ያክላል።
የመጀመሪያው የገጠር ቀበሌ ማዕከላትን ማቋቋም የሚያስችል ፕላን ማዘጋጀት እንደሆነ በሚኒስቴሩ የመሬትና ካዳስተር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ብዙአለም አድማሱ ተናግረዋል።
የተዘጋጀውን ፕላን መሰረት ያደረጉ ቤቶች በተለያዩ ክልሎች መገንባት መጀመራቸውን የሚናገሩት አቶ ብዙአለም በተለይ በኦሮሚያ እና አማራ ጥሩ የሚባል ስራ መኖሩን ጠቅሰዋል።
ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶች የሚገነቡባቸው የገጠር ቀበሌ ማዕከላት ውሎ አድሮ ከተማ መሆናቸው አይቀርም የሚሉት ስራ አስፈጻሚው ሰዎች የሚፈልሱበት ምክንያትም አብሮ እንደሚቀንስ ተናግረዋል።
ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት በኢትዮጵያ ወደ 25 በመቶ እንደሚጠጋ ተነግሯል።
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s