ነሀሴ 22 2017 - ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የመንግስት ተቋማት ምዘና በማድረግ አገልግሎታቸውን ማሻሻል ይችላሉ ተባለ።
- sheger1021fm
- Aug 28
- 1 min read
በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት እንዲሁም ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የመንግስት ተቋማት ምዘና በማድረግ አገልግሎታቸውን ማሻሻል ይችላሉ ተባለ።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዓለም አቀፍ የጥራት መለኪያ መስፈርቶችን መሠረት አድርጎ ባዘጋጀው የልህቀት ሞዴል በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ስር የሚገኙ 19 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለመመዘን እና በጥራት ጉዳዮች ላይ ከተቋሙ ጋር አብሮ ለመሥራት ዛሬ ስምምነት አስሯል።
ስምምነቱ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በቅርንጫፎቹ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ በመመዘን የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታትና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት በገለልተኛ አካል የሚደረግ ምዘና አስፈላጊ መሆኑን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ ተናግረዋል።

አገልግሎቱ ከዚህ ቀደምም ከኢትዮጵያ የጥራት ልማት ሽልማት ድርጅት ጋር የተወሰኑ ቅርንጫፎቹ ምዘና ላይ ሲሰራ እንደነበርና አሁን ግን የጥራት እና አገልግሎት አሰጣጥ ምዘናውን በ19 ቅርንጫፎቹ ላይ ለማድረግ ተሰናድቷል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት አለም አቀፍ የጥራት መመዘኛ መስፈርቶችን በማዘጋጀት ተቋማት አገልግሎቶቻቸውንና ምርቶቻቸውን እንዲያሻሽሉ እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ የሚነሱባቸውን ችግሮች በማሻሻል ህብረተሰቡ የተሟላና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኝ እየሰራ ነው ሲሉ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ መብራት ተናግረዋል።
በኢትዮጽያ የጥራት መመዘኛ ማድረግ በግል እንጂ በመንግስት ተቋማት አልተለመደም ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ገለልተኛ በሆነ አካል በመመዘን አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያሉትን ችግሮች ለመለየት እና ማሻሻያ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።
ተቋማት በራሳቸው ፍላጎት አገልግሎታቸውን በገለልተኛ አካል በመመዘን ያሉባቸውን ክፍተቶች በመለየት ማሻሻያ ማድረግ እንደሚችሉ ተነግሯል።
የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት ጥራት ያለው ምርት እና አገልግሎትን ለማበረታታት መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ የተቋቋመ ድርጅት መሆኑ የተነገረ ሲሆን ይህንኑ ዓላማ ለማሳካትም የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት በበላይ ጠባቂነት ይመሩታል፡፡
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s








